የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕይን በይፋ ከፍተዋል፡፡
በታዳሽ ትራንስፖርት እና የታዳሽ ትራንስፖርት መሠረት ልማት ላይ ትኩረትን ያደረገው ይህ ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሁዋንጃን የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ነው የተከፈተው።
በመርኃ ግብሩ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተገኝተዋል፡፡
ከዐውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በዘርፉ የተሠማሩ ከአለም አቀፍ ተቋማት የተገኙ ባለድርሻ አካላት በታዳሽ የትራንስፖርት እና የዘርፉ መሠረተ ልማቶች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ።
የኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመገንባት በሁሉም ዘርፎች የተጀመረው ሥራዎችን ለማስቀጠል በትራንስፖርት ዘርፍ የተጀመረው ተግባራት ይደግፋል ተብሏል።
በዝግጅቱ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተሠማሩ የዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች፣ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በትዕግስቱ ቡቼ