ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ተምሳሌት መሆኗን የአለም ባንክ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚሪያም ሳሊም ገለፁ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከዓለም ባንክ ካንትሪ ዳይሬክተርና ልኡካን ቡድናቸው ጋር በጤናው ዘርፍ በትብብር በሚሰሩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በኮቪድ ወረርሽኝና በግጭት ጊዜም ቢሆን የአለም ባንክ ድጋፍ እንዳልተለያት በማንሳት የጤና ሚኒስቴርና እና የዓለም ባንክ ትብብር የጤናው ዘርፍ አጀንዳን በፍጥነት ወደ ፊት ለማራመድ ማስቻሉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ከአለም ባንክ ጋር በትብብር እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለማፋጠን ያለውን ዝግጁነት ያብራሩት ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ በዚህ ረገድ የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር ላይ በትብብር መስራት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፤ የወባ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ከአለም ባንክ ጋር በቅርበት ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስቴር በተለይም የእናቶችና ህጻናት ጤናን በማሻሻል ረገድ ያስመዘገበውን ውጤት ያደነቁት የአለም ባንክ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚሪያም ሳሊም፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ተምሳሌት እንደሆነች ተናግረዋል።
በተጨማሪም የጤና መድህን፣ ክትባት፣ ጽዱ ፕሮጀክት፣ የመድሃኒት አቅርቦትን እና የሃገር ውስጥ የመድሃኒት ምርትን ማሳደግ ላይ ተወያይተዋል።
የልኡካን ቡድኑ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክትን፣ እና በአለም ባንክ ድጋፍ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ላብራቶሪን መጎብኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።