በደቡብ ሱዳን የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለጉዳት ዳርጓል

1 Mon Ago 427
በደቡብ ሱዳን የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለጉዳት ዳርጓል

አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል ባዳረሰው የጎርፍ አደጋ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስታውቋል።

በሀገሪቱ ሰሞኑን የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የውሃ ሙላት እና ጎርፍ በአብዛኛው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ይላል የኦቻ መግለጫ።

በሀገሪቱ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በአደጋው ለተፈናቀሉት እና ኮረብታማ ቦታዎች እየሰፈሩ ላሉት ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንዳደረገው ተገልጿል።

ከ11 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ሀገሪቱን በቅርብ አስርት ዓመታት ካጋጠሟት የጎርፍ አደጋዎች የአሁኑ የከፋ ነው ተብሏል።

አሁንም የጎርፍ አደጋ በተጋረጠባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች “ለደህንነታቸው ሲሉ በየአካባቢያቸው ወዳሉ ኮረብታማ ቦታዎች እንዲሸሹ» የሀገሪቱ መንግሥት እያሳሰበ ይገኛል።

በሀገሪቱ ከባድ ዝናብ መጣል ከጀመረ ወዲህ 15 መተላለፊያ መንገዶች አገልግሎት መስጠት በማቆማቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙት እና ግማሽ ሚሊዮን ለሚደርሱት ተጎጂዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ አለመቻሉን ኦቻ ገልጿል።  

የአሁኑ አደጋ የተከሰተው ደቡብ ሱዳን በጎረቤት ሱዳን ለ18 ወራት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለባትን ተፅዕኖ ለመቋቋም ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ጀምሮ በደቡብ ሱዳን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ተመዝግበዋል።

ደቡብ ሱዳን ቀድሞውንም በከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ያለው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)፤ ለአደጋው ምላሽ የመስጠት አቅሟ ይበልጥ እየተዳከመ ነው ሲል አስጠንቅቋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top