በኢትዮጵያ በየዓመቱ ኅዳር 12 የሚከናወነው ኅዳር ሲታጠን ከገጠር እስከ ከተማ ቆሻሻ የማቃጠል ባሕል ለብዙ ዓመታት እየተካሄደ የቆየ ነው።
በየዓመቱ ኅዳር 12 ቆሻሻን ሰብስቦ የማቃጠል እና አካባቢን የማፅዳት ስራ እንዴት ተጀመረ? ለምንስ ይተገበራል? የሚሉ ጥያቄዎችም አብረውት ይነሳሉ። መልሱን በታሪክ ሰፍሮ እናገኘዋለን።
በወቅቱ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተስፋፍቶ የነበረው “ስፓኒሽ ፍሉ” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በ1908 ዓ.ም ኅዳር ወር ላይ የተጀመረው ቆሻሻን የማቃጠል ሥነ-ሥርዓት ዛሬም ድረስ እየተተገበረ ይገኛል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት በላይ ኅዳር 12 እየተጠበቀ የሚከናወነው ቆሻሻን የማቃጠል ስርዓት “ስፓኒሽ ፍሉ” በተለምዶ “የኅዳር በሽታ” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ “አካባቢያችን በመቆሸሹ ምክንያት ነው የተከሰተው” በሚል በሽታውን ለማጥፋት ታስቦ ቆሻሻ ማቃጠል እንደተጀመረ ይናገራሉ።
ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት እየተላለፈ በወቅቱ አልጋ ወራሽ የነበሩትን አፄ ኃይለስላሴን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎችም በበሽታው ተጠቅተው እንደነበር በታሪክ ማስረጃ መስፈሩንም አስታውሰዋል። እናም ይህን ክስተት መሰረት አድርጎ የተጀመረው ኅዳርን የማጠን ሥርዓት በሽታው ከጠፋ በኋላም መቀጠሉንም ያስረዳሉ።
ኅዳር 12 የሚካሄደው ቆሻሻን የማቃጠል እና የአካባቢ ንፅህናን የመጠበቅ ልምድ ዓመት ሙሉ የሚከወን እንዲሆን መሰረት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ አዲስ አበባ ኅዳር ሲታጠንን ዓመቱን ሙሉ እየሰራች ውብ ጎዳናዎች እና ምቹ መኖሪያ አካባቢዎችን ገንብታለች። ይህ ስራዋ አሁንም ቀጥሎ ብዙ አካባቢዎች ምቹ እና ለነዋሪዎች ተስማሚ እንዲሆኑ እያደረገች ነው።
የአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ 365 ቀናት ሁሉ ኅዳር 12 ሆነውላታል።ለዚህም ነው እንደስሟ እያበበች እየተዋበች እንደቀድሞው ጊዜ ወረርሽኝ ተከስቶ መፍትሄ ላይ የምትረባረብ ብቻ ሳይሆን አስቀድማ የምትከላከል ከተማ የሆነችው።
አሁን ለኑሮ ምቹ እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ ለአፍሪካውያን የፅዳት ተምሳሌት የከተማ ዓይን ሆና አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ መርጧት የሚመክርባት የዲፕሎሚሲ ማዕከል ሆናለች።
በእያንዳንዱ ቀን ከመኖሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪ ደረጃ ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን በመጠቀም ወደ አየር የሚለቀቀው ጋዝ በሒደት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የአየር ንብረት ለውጥ እንዳስከተለ የባለሞያዎች እውነት ነው።
እንዲህ ያለው ችግር ዓለምአቀፋዊ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ለችግሩ መፍትሄ ያለችውን መስጠት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች አዲስ አበባን የአየር ብክለት ተጋላጭ እንዳትሆን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለዓለም ያሳየችው ድንቅ መፍትሄ ሆኗል።
በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን የምትተክል ሀገር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ቀድሞ የማዘጋጀት ምልክቷ ነው።
አዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውስጥ ስትሳተፍ የአካባቢ ብክለትን ቀድሞ ለመከላከል እና ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ተፈጥሮዎች እንዲኖሩ የማስቻል ህልም ይዛ ነው።በከተማው የውበት እና ፅዳት ስራ ውስጥ የሚታዩ የአረንጓዴ ቦታዎች በታቀደ እና በተጠና መልኩ መዘጋጀት ለዚህ አንድ ማስረጃ ይሆናል።
ዓመቱን ሙሉ የኅዳር ሲታጠን ዓላማን ቀድማ የጀመረችው አዲስ አበባ ታዲያ በየዓመቱ ኅዳር ሲታጠንን እንዴት ማካሄድ አለበት? ብሎ መጠየቅ አይቀርም።
ቆሻሻን ከማስወገጃ መንገዶች አንዱ የሆነው በአንድ ጊዜ ቆሻሻን ማቃጠል ወደ አየር ለሚለቀቅ ጭስ ምክንያት ይሆናል።እናም በዚህ ጊዜ ቀኑን ለማስታወስ ተብሎ የሚተገበር ቢሆንም የሚወገደውን ቆሻሻ መለየት ጠቃሚ መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም።
ለማዳበሪያነት የሚውል፣ መልሶ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እንዲሁም ሊቃጠል የሚችለውን በመለየት አካባቢን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማፅዳት አስፈላጊ ስለመሆኑ ባለሞያዎች ይመክራሉ።
በወቅቱ በሽታን ለማጥፋት ነው ተበሎ በዘመኑ መፍትሄ የተባለው በኅዳር 12 ቀን ቆሻሻን የማቃጠል ስራ ዛሬስ በዚሁ መንገድ መቀጠል አለበት ብሎ መጠየቅ ነውር የለበትም።
እንዲህ ካልሆነ በአንድ ቀን ብቻ በሚቃጠለው ቆሻሻ አካባቢን አፀዳን ብለን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋችን አይቀርም።
እናም ኅዳር 12 የፅዳት ቀን ሆኖ ቆሻሻን ለይቶ አካባቢን አፅድቶ የአካባቢ አየርን በማይበክል መንገድ ማከናወን ዘላቂ ለውጥን ያመጣል።
እየተለወጠች በየቀኑ እያበበች ያለችው አዲስ አበባም እንዲህ ያለው ቀን በምን መንገድ ሊከወን ይገባል ማለት ይኖርባታል።ዓመቱን ሙሉ በታቀደ መንገድ የአካባቢ ንፅህና እና ፅዳት ላይ ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መርሀግብሮች ላይ የምትሰራ ከተማ የአንድ ቀን ፅዳት ጥቅም እና ጉዳቱን ካልመዘነችው ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።
ኅዳር 12 በብዙ ቆሻሻ ቃጠሎ ጭስ ታፍኖ መዋሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን ከወቅቱ ተግባር ከዘመኑ እውቀት ጋር የሚሄድ የፅዳት ቀን በማድረግ ዘላቂ ለውጥ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።