የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከእስያ በማገናኘት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ተገለፀ

9 Days Ago 269
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከእስያ በማገናኘት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ተገለፀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከእስያ በማገናኘት የጎላ አበርክቶ እንዳለው የሲንጋፖር የጉዞና ጭነት አገልግሎት ወኪሎች ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር ለሀገሪቱ ለተጓዦች፣ የጉዞና የጭነት አገልግሎት ወኪሎች የማበረታቻ ሽልማት መስጠቱ ይታወቃል፡፡

ኢነርጂያ፣ ሲንጋፖር ፖስት ኃ/የተ/የግ/ ማህበር፣ ኤርሰርቭ ግሩፕ፣ ሲቲስቴት ትራቭል፣ እና ኤር ፍራይት ሲንጋፖር እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት ናቸው።

የሲቲስቴት ተራቭል ዋና ዳይሬክተር አልበርቶ ሆ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር ያዘጋጀው ሁነት አየር መንገዱ ምን ያህል ታላቅና እንዴት ውጤታማ እንደሆነ ለመረዳት አስችሎኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከሲንጋፖር ለማስተሳሰር የሚያደርገው አስደናቂ እንቅስቃሴ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ ከሲንጋፖር የቱሪዝም አጋሮች ጋር በመተባበር የሲንጋፖርን ማህበረሰብ ማሳተፍና ከንግድ ባለፈ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሥፍራዎች እንዲጎበኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በሲንጋፖር የኢትዮጵያ ተወካዮች በገበያ እና ከጉዞ ወኪሎች ጋር በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፤ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጋራ የጉዞ ፓኬጅ እንደሚያዘጋጅም አመልክተዋል።

የሲንጋፖር ኤር ፍራይት ዳይሬክተር ካሪል ፋን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ኢትዮጵያ ምን ያህል ማራኪ አገር እንደሆነች አይቻለሁ፤ ለመጎብኘትም ጓጉቻለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ እና ሲንጋፖር መካከል ትስስር በመፍጠር የሚያደርገውን ግስጋሴም አድንቃለሁ፤ የባህል ትብብርን ያሳድጋልም ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ በአፍሪካ ትልቁና በፍጥነት እያደገ ያለ መሆኑን ገልጸው፤ የጭነት ፍላጎቶች በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።

የኤርሰርቪስ ግሩፕ ኮሜርቪያል ማናጀር ክሎኤ ሊም፤ አየርን መንገዱ ከአስር ምርጥ የጎዞ ወኪሎች ይመድበናል ብለን አልጠበቅንም ነበር ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ A350-1000 በቅርቡ ማስገባቱ የአየር መንገዱን አቅም የሚጨምር፤ለተለያዩ ወደ ኢትዮጵያና አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች አህጉራት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሲንጋፖር ፖስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ቪስነሽ ናጋራጃን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከእስያ በማገናኘት የጎላ አበርክቶ አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እምቅ አቅም ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ትብብራችንን የበለጠ ማጠናከር እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሲንጋፖር የጉዞና የጭነት አገልግሎት ወኪሎች፤ የአየር መንገዱ የሰፋ መዳረሻ በተለይ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት ደንበኞችን ወደ መነሻ ስፍራ መውሰድ ያስችላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲንጋፖር፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ ቀጣናዊ ሥራ አስኪያጅ ተሊላ ደረሳ፤ የጉዞ ወኪሎቹ ዘመናዊ የጉዞና የካርጎ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ፤ለቱሪዝም፣ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል።

የሲንጋፖር መስመር በእስያ አህጉር ካሉ ምርጥ እና አትራፊ የንግድ መስመሮች አንደኛው መሆኑን አመልከተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካና እስያ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ ንግድ፣ እና የባህል ልውውጥን ለማሳደግ እንደ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top