የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት ስራን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር የመልሶ ልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።
በዓለም አቀፉ የጁገል ቅርስ ካሁን ቀደም የተከናወኑ የኮሪደር የመልሶ ልማት ስራዎችን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ቅርሶች የሚገኙባት ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ዓለም አቀፍ ቅርሱ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን የሚመሩበት ሕያው ሙዚየም መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
ቅርሱ ቋሚ ጥበቃ እና እንክብካቤ የሚያስፈልገው በመሆኑ ለኮሪደር ልማቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት የቅርስ ጥበቃ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።
ከዚህ ቀደም በቅርሱ ብሎም በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣የአረንጓዴ ልማት፣ፅዳትና ውበት ስራዎች አካባቢውን ለነዋሪው ብሎም ጎብኚዎች ምቹ በማድረግ የቱሪዝም ፍሰቱን ማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል።
በቀጣይም የተስተዋሉ ውስንነቶችን በማረም የኮሪደር ልማቱን በጥራት እና ፍጥነት በማከናወን የቅርስ ጥበቃ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።