የሚያስቆጨው ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት ኃብት

1 Day Ago 112
የሚያስቆጨው ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት ኃብት

በዓለም ላይ ከሚገኘው ከ35 ሺህ በላይ የዓሣ ዝርያዎች ውስጥ 200 የዓሳ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ::

የብሄራዊ የዓሣና የውኃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጋሻው ተስፋዬ ኢትዮጵያ እምቅ የዓሳ ሀብት መገኛ ነች ብለዋል፡፡

ሃገሪቱ በሀይቆችና ወንዞች በዓመት እስከ 73 ሺህ ቶን፤ በዓሳ ግብርና ደግሞ 2 ሺህ ቶን ብቻ ዓሳ እያመረተች መሆኑን ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል::

የብሄራዊ የዓሳና የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል የዓሳ ሀብትን ለመጠቀም የሚያግዙ ዘዴዎችን በምርምር የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል::

ማዕከሉ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሁለት የተለያዩ የቆሮሶ የዓሳ ዝርያዎችን በማዳቀል የሚፈለገውን ወንድ የቆሮሶ ዓሣ ጫጩት ብቻ ለማስፈልፈል የሚያሥችል የምርምር ሥራ መስራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል::

ይህም 75 በመቶ ወንድ የዓሳ ጫጩት ማራባት የሚያስችል የምርምር ውጤት እንዲገኝ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል::

በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ምርት ለማግኘት የሚያስችል የመኖ ቴክኖሎጂ ምርምር ሙከራም እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል::

በማዕከሉ የዓሳ ተማራማሪ አቶ አለማየሁ ውቤ፤ እንደ ሙቀቱ መጠን ከ4-6 ቀን በቤት ውስጥ የዓሣ ማስፈልፈያ ተክኖሎጂ በመጠቀም ከቆሮሶ ዓሳ እንቁላል ተወስዶ የማስፈልፈል ስራ ይሰራል ብለዋል::

ማዕከሉ ከኔዘርላንድ ባስመጠው ዘመናዊ የዓሳ ማባዣ (ማስፈልፈያ) መሳሪያ ከ1 እስከ 2 ወር ውስጥ "ዱባ" እና "ቆሮሶ" ዝርያዎችን ጫጩት በማባዛት ፍላጎት ላላቸው እያሰራጨ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የውሃ አካላት በዓመት 130 ሺህ ቶን ዓሣ ታመርታለች::

የግብርና ዘዴን በመጠቀም ደግሞ 400 ሺህ ቶን የምታመርት ሲሆን በድምሩ ከ530 ሺህ ቶን ዓሣ የማምረት እምቅ ኃብት እንዳላት የብሄራዊ የዓሣና የውኃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል መረጃ ያመላክታል::

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top