የተጠበቀውን ያህል አገልግሎት እየሰጠ ያልሆነው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር

3 Hrs Ago 47
የተጠበቀውን ያህል አገልግሎት እየሰጠ ያልሆነው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር
የከተማዋን ነዋሪዎች የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ዓላማ አድርጎ ከ475 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎበት ስራ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ በታሰበው መጠን ችግሩን መፍታት እንዳልቻለ ይነሳል።
 
በከተማዋ በተዘረጉ የባቡር መስመሮች የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች ውስንነት እና የሚያጋጥሙ ተደጋጋሚ ብልሽቶችም የቅሬታ መነሻ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡
 
የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቱ ካሉት 40 በላይ ባቡሮች በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ከ50 በመቶ በታች መሆናቸው ተነግሯል።
ኢቲቪ ያነጋገራቸው የባቡር ተጠቃሚዎችም በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያላቸውን ቅሬታ አንስተዋል፡፡
 
ይህንን መነሻ በማድረግ የዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን 'የሀገር ጉዳይ' መሰናዶ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይን አጀንዳ አድርጓል፡፡
 
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖር አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ብርሀን አበባው (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የከተማዋ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በታሰበው ልክ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ ተናግረዋል።
 
ዋና ስራ አስፈጻሚው ለዚህም በዋና ምክንያትነት ከመነሻው ጀምሮ የመለዋወጫ እቃ እጥረት መኖሩን ነው የሚያነሱት፡፡
ደረጃውን የጠበቀ የጥገና ወርክሾፕ አለመኖሩም ሌላው ምክንያት እንደሆነ አክለዋል፡፡
 
ባቡሮቹ የሚያጋጥማቸው የጊዜ መዘግየት እና የመቆራረጥ ችግርም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ነው የሚጠቅሱት፡፡
 
አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ልዩ ትኩረት ባለፉት 6 ወራት 5 ባቡሮች ተጠግነው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን የሚናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በዚህም አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮችን ቁጥር ወደ 18 ከፍ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል፡፡
 
አሁንም የትራንስፖርት አገልግሎቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት፡፡
 
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ በበኩላቸው፤ ስራው ሲጀመር የቀላል ባቡር መሰረተ ልማት መስራትና ስራ ማስጀመር፣ የኪሎሜትር ሽፋንን ማስፋት እና ደረጃውን የጠበቀ የጥገና ወርክሾፕ ሟሟላትን መሰረት ያደረገ እንደነበር አንስተዋል።
 
ሆኖም ግን የቀላል ባቡርን መሰረተ ልማት ከመስራትና ስራ ከማስጀመር በዘለለ ሌሎች ተግባራት አለመከናወናቸው ለችግሩ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በቀጣይ የጥገና ወርክሾፖችን እና የመለዋወጫ እቃዎችን በሟሟላት አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች ቁጥር እንዲጨምር እና አገልግሎቱ እንዲሣለጥ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ እና የቻይና መንግስት በጉዳዩ ላይ ጥናት እያካሄዱ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በጥናቱ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል፡፡
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top