በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በሬክተር ስኬል 5 ሆኖ የተመዘገበ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ተሰምቷል፡፡
በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በአዲስ አበባ ተደጋጋሚ የመሬት ንዝረት መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ለ EBC DOTSTREAM አረጋግጠዋል።
በዚህ ሳምንት በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ኤሊያስ፤ ምሽቱን በሬክተር ስኬል 5 ሆኖ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ መሰማቱን ተናግረዋል።
በአካባቢው ያለው የቅልጥ ዓለት ድንጋይ (ማግማ) እንቅስቃሴ አሁንም በመቀጠሉ የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እንዲከሰት ማስቻሉን ዶ/ር ኤሊያስ ጨምረው ገልጸዋል።