የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለፉት 6 ወራት 597 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና መግባታቸው ተገልጿል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመትና የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የግምገማ መድረክ የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት አባላት እና የመምሪያ ኃላፊዎች በተገኙበት በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ በዚሁ ወቅት፤ ከ 80 በላይ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ኮርፖሬሽኑ ወደ ሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች መሳባቸውን ገልጸዋል።
በተሳቡት ኢንቨስትመንቶች 14 የማምረቻ ሼድና ከ 70 ሄክታር በላይ የለማ መሬት ለባለሃብቶቹ መተላለፋቸውን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ኢንቨስትመንቶቹ በመቀሌ፣ በቦሌ ለሚ፣ በቂሊንጦ፣ በኮምቦልቻ፣ በድሬዳዋ ልዩ ነፃ ንግድ ቀጠና፣ በጂማና ሰመራ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ዉስጥ የሚሰማሩ መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ከተሳበዉ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ዉስጥ የቻይና፣ የሩሲያ፣ የቬትናም እና የአገር ዉስጥ ባለሀብቶች ሲሆኑ በፋርማሲዩቲካል፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ በተለይም ቡናና ሻይ፣ በኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠም እና ሌሎችም የቴክኖሎጂና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የሚሰማሩ መሆናቸውን አቶ ዘመን ጨምረው ገልጸዋል፡፡