የአፍሪካ ሕብረት የልማት ድርጅትን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ እ.አ.አ በ2022 በተካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ጉባኤ ከሕብረቱ አባል ሀገራት ሙሉ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡ በዚህም የቀድሞውን ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂም አሳን ማያኪን ተክተው የኔፓድ ዋና ዳይሬክተርነት ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡
በኃላፊነት በሠሩባቸው ተቋማት ትብብርን በማሳደግ እና በስትራቴጂካዊ የአመራር ስልታቸው ለውጥን እና ዘለቄታዊ ዕድገትን በማምጣት አቅማቸው ይታወቃሉ።
በኬንያ የተመድ ተወካይ ሆነው በሠሩበት ወቅት የሀገሪቱን ህገ-መንግሥት ሪፎርም በመሥራት፣ የሰላም ተቋማት እንዲጠናከሩ በማስቻል፣ ከራስ ወዳድነት በጸዳ አገልግሎታቸው፣ የኬንያ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ግጭቶችን በመፍታት ብቃታቸው ከበርካታ የኬንያ ተቋማት ዕውቅና እና የሰላም ሽልማቶችን አግኝተዋል።
የኬንያ ምርጫን ተከትሎ እ.አ.አ በ2007/08 ለተቀሰቀሰው ዓመፅ መፍትሔ ለማግኘት ሲቪል ማኅበረሰብን፣ የግል ድርጅቶችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ አሰባስበው ዘላቂ መፍትሔ እንዲገኝ አድርገዋል።
የአሁኗ የኔፓድ ዋና ዳይሬክተር ናርዶስ በቀለ የተወለዱት በ1951 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲሆን፣ ለቤተሰባቸው አምስተኛ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን፣ በጎንም የንግድ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት የቤተሰቦቻቸውን ንበረት ከመውረሱም በላይ ሁለት ልጆቻቸውን ገድሎባቸዋል፡፡
ስለቤተሰቦቻቸው ሲናገሩም፣ "ያደኩት ፍቅርና መተሳሰብ በሞላበት ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ወላጆቼ የትምህርትን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው እያስረዱን ነው ጥብቅ በሆኑ የሥነ ምግባር እሴቶች እና በኃላፊነት ያሳደጉን፤ የመከባበር፣ ጠንክሮ የመሥራት እና ሰዎችን መርዳት አስፈላጊነት አስተምረውናል” ይላሉ፡፡
በአብዮቱ ቤተሰቦቻቸው ላይ ስለደረሰው ምስቅልቅል ሲገልጹም፣ "ከአብዮቱ በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ፤ መላው ቤተሰብ ፈታኝ ችግር እና ፍርሃት ላይ ወደቀ በመጨረሻም ሁለቱን ወንድሞቼ ተገደሉብኝ፤ ሁኔታው በጣም አሰቃቂ ነበር" በማለት ያስታውሱታል፡፡
በ18 ዓመታቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በመሰረተ ትምህርት መሀይምነትን ለማስወገድ ሲደረግ በነበረው እንቅስቃሴ ወደ ሞያሌ ዘመቱ። ያጋጠሟቸው አሳዛኝ ሁኔታዎች እና የሁለቱ ወንድሞቻቸው ትዝታ ቀን እና ሌሊት አእምሮአቸውን እያስጨንቃቸው ቢሆንም በቁርጠኝነት ወደፊት መሄድ ግድ እንደሆነ ተረድተው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። ይህን ጉዳይ ሲያነሱም፣ "በ1968 ዓ.ም መሀይምነትን ለማጥፋት ሲካሄድ በነበረው የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ወደ ሞያሌ ሄድኩ፤ እዚያ ለአንድ ዓመት ያክል የቆየሁ ሲሆን፣ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ አልፌአለሁ፤ ያ አጋጣሚ አስተሳሰቤን በተወሰነ ሁኔታ ለውጦት ነበር፤ ሞያሌ የነበረውን ሁኔታ አስቸጋሪ ነው ካልኩት የኔ አኗኗር ጋር ሳነጻጽረው ልዩነቱ ሰፊ መሆኑን ተረዳሁት፤ ሁኔታው ያገኘኋቸውን አጋጣሚዎች እና ያገኘኋቸውን በረከቶች ማድነቅ እንድጀምር አደረገኝ፤ ሰዎችን መርዳት እንዳለብኝም ለራሴ ቃል ገብቼ በቆይታዬ የምችለውን ያደረኩትም በዚያ ምክንያት ነው" ብለዋል፡፡
የመሰረተ ትምህርት ዘመቻቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ በ1974 ዓ.ም በኢኮኖሚ እድገትና እቅድ፣ በአፕላይድ ስታቲስቲክስ እና ፖለቲካል ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ በተመድ ልማት ድርጅት የአዲስ አበባ አገናኝ ቢሮ ውስጥ የመሰረታዊ ሂሳብ፣ ስታቲስቲክስ እና ምርምር ረዳት ሆነው ሠርተዋል፡፡ የተመድ ልማት ድርጅት የቀጣናው ፕሮግራም ዋና የቴክኒክ አማካሪ ረዳት እንዲሁም የውሃ ሀብት እና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል፡፡
ወደ ኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ በማምራትም በ1977 ዓ.ም በኢኮኖሚ ልማት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አገኙ። በ1979 ዓ.ም የተመድ ልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ወደ ህንድ ተጓዙ፡፡ ይህም የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሥራ ልምዳቸው ነበረ።
ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮሞሮስ ደሴቶች፣ ቤኒን፣ ኡጋንዳ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ህንድ እና ኒውዮርክ ባሉ ሀገራት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ተመድን እና የልማት ድርጅቱን ወክለው ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል። እንደ ኬንያ ብዙ ዓመት የሠሩበት ሀገር እንደሌለ እና ኬንያ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ሥራዎችን መሥራታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በእነዚህ ሀገራትም በተመድ ውስጥ በተለያዩ ያኃላፊነት ደረጃዎች ውጤታማ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በኒው ዮርክ የተመድ ዋና ፀሐፊ ቢሮ ጽሕፈት ቤት ጠቅላላ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የዋና ፀሐፊውን እና የምክትሉን እንዲሁም የካቢኔ ጉዳዮችን የማስተዳደር ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል። በኬንያ የተመድ ቢሮ አስተባባሪ እና የተመድ ልማት ድርጅት ተወካይ ሆነው ሠርተዋል። እ.አ.አ ከኅዳር 2008 እስከ መስከረም 2013 በቤኒን ሪፑብሊክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢሮ አስተባባሪ እና የተመድ ልማት ድርጅት ተወካይ ሆነው አገልግለዋል።
በዚህ ልምዳቸውም ነው ኔፓድን እንዲመሩ በሙሉ ድምጽ የተመረጡት፡፡ ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት ከ40 ዓመታት በላይ ባካበቱት ልምዳቸው የአፍሪካን የልማት አጀንዳ ወደ ፊት ለማራመድ ጠንካራ እና ቁርጠኛ አመራር እንደሚሰጡ የሕብረቱ አመራሮች ይተማመኑባቸዋል። በተለይም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እና በአጀንዳ 2063 ቁልፍ ዓላማዎችን ለማሳካት ሁነኛ ሰው እንደሆኑ ነው አቅማቸውን የሚያውቁ ሰዎች የሚናገሩት።
የኔፓድን ኃላፊነት ሲረከቡም፣ "የሀገራቱን መሪዎች፣ የኔፓድ አመራር ኮሚቴ አባላት እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ድጋፍ ትልቅ መሆኑን መመልከት የሚያበረታታ ነው፤ ሙሳ ፋኪ መሐመድን እና ሁሉንም የሕብረቱን ኮሚሽነሮች ላመሰግን እወዳለሁ፤ የኔፓድ ዋና ዳይሬክተር በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፤ የሚጠበቅብኝን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመወጣትም ዝግጁ ነኝ” ብለው ነበር፡፡
ናርዶስ በቀለ የዋና ዳይሬክተርነቱን ከተረከቡ በኋላ በፍጥነት ነው ወደ ሥራ የገቡት። ዋና ኃላፊነታቸውም ሕብረቱ እ.አ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብሎ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የያዛቸውን ታላላቅ ራዕዮች እውን እንዲያደርግ ማስቻል ነው።
የአፍሪካ ሕብረት የቴክኒክ አካል የሆነው ኔፓድ ድርሻው የፕሮጀክችን እቅድ ማዘጋጀት፣ ቴክኒካዊ እርዳታ ማድረግ እና ለአባል ሀገራት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ ናርዶስ ይህን ኃላፊነታቸውን በብቃት እየተወጡ እንደሆነም ይነገራል።
ናርዶስ የታዋቂ አፍሪቃ ሴቶች ቡድን አባል ናቸው፡፡ ከላይቤሪያ ፕሬዝዳንት እና ከቀድሞ የማላዊ ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን የ"2015 የግሩም ሴት” ከፍተኛ ሽልማት ተቀብለዋል። እ.አ.አ በ2007ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአፍሪካ ዘላቂ የሰው ልማት ባበረከቱት አስተዋፅኦ እና የመሪነት ሚና ‘ሊቪንግ ሌጀንድ’ ተብለው የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። እ.አ.አ በ2010 "የፌዴሬሽን ለሰላም" የክብር ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።
በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና ሞኖግራፎችን ያሳተሙ ሲሆን፣ አማርኛ፣ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ከሥራ እና የጽሑፍ ቋንቋዎቻቸው መካከል ናቸው።
እ.አ.አ በ2024 ኒው አፍሪካን መጽሔት ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን መካከል አንዷ ናቸው ብሏቸዋል፡፡ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ቀጣናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲስፋፋ እና የወጣቶች ሥራ አጥነት እንዲቀንስ የክህሎት ሥልጠናዎች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራታቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እንደሚያጎላው በመጽሔቱ ላይ የወጣው መረጃ ያመላክታል።
ናርዶስ ስለራሳቸው ሲናገሩ ጥሩ ጓደኞችን ማፍራት የሚወዱ ማኅበራዊ ሰው መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከወጣቶች እና ሴቶች ጋር ፎረም ማዘጋጀት እና ስለ ዕድገት መወያየት እንደሚያስደስታቸው ያወሳሉ። በተጨማሪም ከቤተሰባቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታቸው ይጠቅሳሉ።
ስለ ህይወት ልምዳቸው ሲያወሱም፣ "በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝ ተሞክሮዎች በጣም አስፈላጊ እና አስተማሪ ናቸው፤ የተወለድኩት ሁሉም ነገር በተሟላለት ነገር ግን ሁለት ሁለት ልጆቻቸውን ጨምሮ ሁሉም ነገር በአንድ ቀን በተወሰደበት ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ያ ሁኔታም ያለን ነገር ዘላቂ እንዳልሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል፤ ነገር ግን የሌሎችን ሕይወት እንዴት እንደምንለውጥ እና በልባቸው ውስጥ የምንቀርጸው ነገር ለዘላለም የሚታወስ መሆኑንም ተምሬበታለሁ" ይላሉ፡፡
ለሚ ታደሰ