ጋና ሁሉም አፍሪካውያን ዜጎች ያለቪዛ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ ፈቀደች

14 Hrs Ago 62
ጋና ሁሉም አፍሪካውያን ዜጎች ያለቪዛ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ ፈቀደች
የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አድዶ ዳንክዋ አኩፎ-አዶ የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ያለቪዛ ወደ ጋና የሚገቡበትን ፈቃድ ሰጥተዋል።
 
የቪዛ ነጻ የጉዞ ፖሊሲው የአፈጻጸም ፈቃድ ባለፈው ሳምንት እንደተሰጠ ዝርዝር መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል፡፡
 
ከ2025 መጀመሪያ ወራት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ፖሊሲው፣ ጋናን ሁሉም የአፍሪካ ፓስፖርት የያዙ ዜጎች ያለቪዣ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የፈቀደች አምስተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ያደረጋታል።
 
ከዚህ ቀደም ሩዋንዳ፣ ሲሼልስ፣ ጋምቢያ እና ቤኒን የአፍሪካ ፓስፖርት የያዙ ሀገራት ከቪዛ ነጻ ወደ የሀገራቸው እንዲገቡ የፈቀዱ ሀገራት ናቸው።
 
ፈቃዱ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በኩል ከአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ ውህደት ራዕይ ጋር የሚናበብ እንደሆነም የጋና ዌብ ዘገባ ያመላክታል።
 
ይህ እርምጃ 55 ሀገራትን ያካተተውን የዓለማችን ትልቁን ገበያ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ እና በአፍሪካ መንግሥታት እና በንግድ ድርጅቶች መካከል ያለውን ትብብር እንደሚያጎለብት ይጠበቃል።
 
ፕሬዚዳንቱ ፖሊሲውን ሲያጸድቁ ባደረጉት ንግግር፣ "ግባችን የአፍሪካን ብልፅግና እውን ማድረግ፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ምርቶች ላይ እሴት መጨመር እና ንግድን ማስፋፋት ነው" ብለዋል፡፡
 
የአጀንዳ 2063 ፕሮግራሞችን ለማሳካት "በፓን-አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ፣ በአፍሪካ የህዳሴ ራዕይ ላይ የተመሰረተ እና የተዋሃደ አህጉር እውን ማድረግ" እንዲሁም "ጠንካራ ባሕላዊ ማንነት፣ የጋራ ቅርስ፣ የጋራ እሴት እና ሥነምግባር ያላት አፍሪካን እውን ማድረግ" አስፈላጊ እንደሆነ የአፍሪካ ሕብረት ፕሮግራም ያመላክታል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top