ከሐዋሳ ጎዳናዎች ጠፍተው አያውቁም። የእሳቸው መኖሪያ መንደር የት እንደሆነም አይታወቅም። በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች የተቦረቦረ አስፓልት ኮረት ድንጋይ ሰብስበው ሲደመድሙ፤ የፈረሰ ኮብልስቶን ንጣፍ ሲያስተካክሉ ነው እዚህም እዚያም የሚታዩት።
የሐዋሳ ከተማ ነዋሪው አቶ ጌታቸው ገብረሚካኤል ላለፉት በርካታ ዓመታት በየዕለቱ ለአንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ ያህል በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የበጎ ፍቃድ ስራ ያከናውናሉ።
ሐዋሳ ከተማ እንደ ዛሬው መልከ ብዙ የትራንስፖርት አማራጮች ባልተስፋፉበት ጊዜ ፈረስ እና ጋሪ ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ ዋነኛ የትራንስፖርት አመራጭ ሆኖ በስፋት አገልግሏል።
የዛሬ በጎ ፈቃደኛ ባለ ታሪካችን የዚያ ዘምኑ እንግልት የበዛበት የፈረሶች ድካም ልባቸውን አራርቶት ለበጎ ፍቃድ ስራቸው መነሻ ሆኗቸዋል።
ጋሪ የሚጎትቱ ፈረሶች እንደባለቤቶቻቸው የልብ ፈቃድ ላይ ታች ሲመላለሱ የተቦረቦረ መንገድ ሲገጥማቸው እና ለመሻገር ሲቸገሩ ተመልክተዋል።
ፈረሶቹ ከነጭነታቸው ገብተው ለመውጣት ከመቸገራቸው በላይ ባለ ጋሪዎች ችግሩ የመንገዱ መሆኑን ባለማስተዋል ፈረሶቹ የለገሙ እየመሰላቸው ክፉኛ ሲገርፏቸው፤ የፈረሶቹ ህመም ልባቸው ድረስ ዘልቆ ተሰምቷቸዋል። ይህ ሁኔታ ሩህሩህ ልባቸውን አነሳስቶት ፈረሶቹን መርዳት ከቻልኩ ብለው የበጎ ፈቃድ ተግባራቸውን እንደጀመሩ ያወሳሉ።
በመንገዳቸው ያገኟቸውን የተቦረቦሩ እና የጎረጎዱ ቦታዎችን በኮረት በመደምደምና በማስተካከል መንግስት በዘላቂነት ችግሩን እስኪፈታ እሳቸው ጊዜያዊ መፍትሄ ይሰጣሉ።
"ገንዘብ ባይኖረኝም በጉልበቴ ለችግሮች መፍትሄ መስጠት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ" የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ በበጎነት ብዙ ጉድለቶችን መሙላት እንደሚቻል አንስተዋል።
"እንስሳት የሰው ልጆች አጋዥ ናቸው። በሬ አርሶ ያበላናል። ውሻም የሰው ልጅ የልብ ወዳጅ ነው። ቤትህ ካደረ ያንተ አበጋዝ ነው፤ ንብረትህን ቤትህን ይጠብቃል። በቀደመው ዘመን ፈረስም እስከ ጦር ሜዳ ዘልቆ ለሀገር ሉዓላዊነት መዋደቁን የኋላ ታሪካችን ያስረዳናል" ሲሉም ይገልፃሉ፡፡
"የእንስሳትን ዋጋ ባለመረዳት ተገቢውን ዋጋ ስንሰጣቸው አላስተውልም ይሄ መስተካከል ይኖርበታል ብዬ አሰባለሁ" የሚል መልዕክትም አላቸው።
ዕለት ዕለት ስለሚተገብሩት እና መገለጫቸው ስለሆነው መንገድ የማስዋብ ስራም ሲጠየቁ፤ "ስራው ለብዙኃን ይጠቅማል፤ ለኔ ግን እንደ መዝናኛ ነው አሁን ልምድ አድርጌው የበጎ ፍቃድ ስራን የህይወቴ አንዱ አካል አድርጌዋለሁ" ሲሉ ለሚሰማቸው በብዙ ድካም ስለሚሰሩት ስራ የሚያወሩ አይመስሉም።
ዜጎች በያሉበት አከባቢ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በበጎ ፍቃድ ቢሰሩ ብዙ ማህበራዊ ችግሮቻችንን እንቀርፋለን።
አብሮነት እና መተሳሰብን በታዳጊዎች ላይ በመዝራት፤ በጎ ፍቃድ ባህል እንዲሆን ብንሰራ ሀገራችን ብዙ ታተርፋለች።
በሚካኤል ገዙ