የኢትዮጵያና የጅቡቲ የደኅንነት ተቋማት በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለመግታት የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁመው ለመሥራት ተስማሙ

1 Day Ago 83
የኢትዮጵያና የጅቡቲ የደኅንነት ተቋማት በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለመግታት የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁመው ለመሥራት ተስማሙ

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የጅቡቲ ሪፐብሊክ የሴኪዩሪቲ ዶክመንቴሽን ሰርቪስ በሁለቱ ሀገራት ድንበሮች አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለመግታት  ከሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ ባሻገር የጋራ ግብረኃይል አቋቁመው ስምሪት ለማከናወንና ወንጀለኞችንም አሳልፎ ለመስጠት መስማማታቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

በጅቡቲ ሪፐብሊክ የሴኪዩሪቲ ዶክመንቴሽን ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ ካይራ የተመራ የልዑክ ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በጅቡቲ ሪፐብሊክ የሴኪዩሪቲ ዶክመንቴሽን ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ ካይራ ከተመራው የልዑካን ቡድን አባላት ጋር በጸጥታ፣ በደኅንነትና በተያያዥ መስኮች ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚረዳ ምክክር ማድረጋቸውን መረጃው ገልጿል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የጋራ ስጋቶች መመከት የሚያስችሉ እንዲሁም ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማምጣት የሚረዱ ጉዳዮች ዋንኛ የምክክሩ አጀንዳዎች እንደነበሩ የጠቆመው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታት፤ ሕገ-ወጥ ስደተኞችንም ለመከላከል የሚደረገውን ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸውን አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ በኩል የምታከናውነው የወጪ ገቢ ንግድ ላይ የሚስተዋሉ የደኅንነት ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ውይይት መካሄዱንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top