የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥራት መሠረተ ልማት ስኬቶች

19 Days Ago 397
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥራት መሠረተ ልማት ስኬቶች

የጥራት መሠረተ ልማት ምንድን ነው?

የጥራት መሠረተ ልማት (QI) የሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ጥራት፣ ደህንነት እና ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተቋማትን፣ ማዕቀፎችን እና አገልግሎቶችን ያካተተ ሥርዓት ነው። ንግድን መደገፍ፣ ፈጠራን ማሳደግ፣ ሸማቾችን ከአደጋ መጠበቅ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ማስፈጸም የጥራት መሠረተ ልማት ዋና ዓላማ ነው።

ወጥነት እና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ የምርቶች ሂደቶች እና አገልግሎቶች አሰጣጥ ደረጃዎችን እና መመሪያዎችን ይደነግጋል፡፡ ዓለም አቀፍ የስታንዳርዳይዜሽን ድርጅት (ISO) እና የአፍሪካ ስታንዳርዳይዜሽን ድርጅት (ARSO) ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ለቤተ ሙከራዎች እና ለምርመራ ተቋማት የምስክር ወረቀት የሚሰጡ ድርጅቶች ከተቋቋሙት መስፈርቶች ጋር የሚስማሙ መሆናችን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው። በፖሊሲ የተደገፉ ደረጃዎችን በማውጣት መስፈርቱን ለሚያሟሉ ተቋማት የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡

ምርቶች ወይም አገልግሎቶች የተወሰነላቸውን መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆን አለመሆናቸውን ይወስናል፤ ማረጋገጫ እና ደረጃም ይሰጣል፡፡ ይህም ቁጥጥር፣ ምርመራ እና ምስክር ወረቀት መስጠትን ያካትታል፡፡ በገበያ ላይ ያሉ ምርቶች አስተማማኝ እና ከመስፈርቶች ጋር ተስማምተው የተመረቱ መሆናችን ይከታተላል ፤ ይቆጣጠራል፡፡

ውጭ የሚላኩ እና ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የምርቶች እና አገልግሎቶች ደህንነት አስተማማኝነት እና ውጤታማነት ዋስትና መስጠት፣ ለጥራት ግልጽ የሆኑ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መሰረት የሚሆኑ ፈጠራዎችን ማበረታታት እና ሥነ-ምህዳራዊ ተስማሚ መስፈርቶችን በማስፈጸም ዘላቂ የሆኑ ተግባራትን ማበረታታት የጥራት መሠረተ ልማት ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡

በፖሊሲ የተደገፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥራት መሠረተ ልማት

ብሔራዊ የጥራት ቁጥጥር መሰረተ ልማት (NQI) ማዕቀፍ ኢትዮጵያ በዘላቂ ልማት እና በኢንዱስትሪ መስፋፋት ላይ ዘላቂ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ በሆነ መንገድ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ለመዋሃድ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የማይተካ ሚና አለው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት (NQI) የኢትዮጵያ ምርቶች እና አገልግሎቶች በሀገር ወስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ የጥራት መሰረተ ልማቶች የኢትዮጵያ ስታንዳርድ ኤጀንሲ (ESA)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት (NMIE) እና የኢትዮጵያ ጥራት ቁጥጥር ኤጄንሲ(ECAE) ናቸው፡፡

የእነዚህ ተቋማት ዓላማ ለምርት እና አገልግሎት መስፈርቶችን በማስቀመጥ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ተቋማት የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠት እና ቀጣይነታቸውን መከታታል ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የጥራት መስፈርቶችን ማዘጋጀት፣ አክሬዲኬሽን፣ የምስክር ወረቀት እና የጥራት ማስፋፊያ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።

ለመሆኑ እነዚህ ተቋማት ምን ምን ተግባራትን ያከናውናሉ?

የፖሊሲ ግብአትን ማቅረብ ከነዚህ ተቋማት ተግባራት መካከል ነው፡፡ በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ የጥራት ምክር ቤት ለመመስረት የሚያስችላትን ፖሊሲ ይፋ አድርጋለች። ይህ ፖሊሲ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ስምምነት (AfCFTA) እና ከዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) መስፈርቶች ጋር የሚጣጣም ነው። በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያስችላል።

ሌላው የእነዚህ ተቋማት ዓላማ አቅም ግንባታ ነው፡፡ ይህም የጥራት ማረጋገጫ ሠራተኞችን ማሰልጠን እና ላብራቶሪዎችን ለካሊብሬሽን እና ለምርመራ ማዘጋጀትን ያካትታል። በ2014 ዓ.ም የምርት እና የአገልግሎት አቅርቦት እንዲሻሻል ለሠሩ እና ምርት እና አገልግሎታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ላሻሻሉ ከ2 ሺህ በላይ ተቋማት አቅም ግንባታ እና ዕውቅና ተሰጥቷል።

የግል ሴክተር ተሳትፎን መጨመር ሌላው የዚህ ተቋም ዓላማ ነው፡፡ የቁጥጥር፣ የማረጋገጫ እና የላቦራቶሪ አገልግሎት መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር የግል ሴክተሩን ተሳትፎ ያሳድጋል፡፡ የግሉ ሴክተር ወደዚህ ዘርፍ እንዲመጣም ማበረታቻዎችን ይሰጣል። ይህም የመንግሥት እና የግል ትብብር የጥራት ማረጋገጫ መዳረሻ እና ቅልጥፍናን ያጎለብታል፡፡

ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር ሌላኛው ዓላማው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥራት ማረጋገጫ መሰረተ ልማት ከፓን-አፍሪካ የጥራት መሰረተ ልማት ፖሊሲ ጋር መስተጋብር የሚፈጥር ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ቀጣናዊ መስፈርቶች አንዲኖሩ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ቁጥጥር መሠረተ ልማት ምን አሳካ?

ብሔራዊ የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ፖሊሲ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ በፖሊሲ የተደገፈው ብሔራዊ የጥራት ቁጥጥር መሠረተ ልማት ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ የወጭ ምርቶች ጥራትን በመጨመር የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነትን እያጠናከረ ነው። ፈጣን እና አስተማማኝ የጥራት ቁጥጥር መሰረተ ልማቶች ለኢንዱስትሪዎች ራስ ምታት የሆነውን የጥራት ማረጋገጫ ሂደቶችን እያቀላጠፈ ነው፡፡ እየተሻሻለ የመጣው የጥራት ቁጥጥር መሰረተ ልማት የዓለም አቀፍ ተቋማትን አመኔታ እየጨመረ በመምጣቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን አያሳደገ ነው፡፡

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top