"ፍትሐዊው ያልተጻፈ ሕግ"- "ሔር ኢሴ"

7 Days Ago 432
"ፍትሐዊው ያልተጻፈ ሕግ"- "ሔር ኢሴ"

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ የተካተቱ በርካታ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት።

አሁን ደግሞ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነ የማይዳሰስ ቅርስ ነው የተባለው የሱማሌ-ኢሳ ማህበረሰቦች የቃል ልማዳዊ ሕግ (ሔር ኢሴ) በ19ኛው የተመድ የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ጉባኤ በማይዳሰሱ የሰው ልጅ ቅርሶች ተወካይ ዝርዝር ውስጥ በዓለም አቀፍ ማህደር ተጽፏል።

ይህ ሕግ (ሔር ኢሴ) ምንድነው?

ኢትዮጵያ ከጉርብትና ውጭ ከሶማሊያና ከጅቡቲ ጋር ሀይማኖት እና ወግ ትጋራለች፤ ለዚህም ነው በነዚህ ሀገራት ተመሳሳይ ክንውኖች ያሉት፤ ከነዚህ የማይዳሰሱ ባሕል፣ ወግና ሕጎች ውስጥ "ሔር ኢሴ " ሦስቱን ሀገራት ያስተሳሰረው ሕግ ሆኖ ይጠቀሳል።

“ሔር ኢሴ” በሦስት የተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የማኅበረሰቡ አባላትን አንድ የሚያደርጋቸውና የሚያስተሳስራቸው የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው የጋራ መተዳደሪያ ባሕላዊ ሕግ ነው ።

የኢሳ ሶማሌ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሕግ ወይንም ሔር ኢሴ ታሪካዊ ዳራ የሚጀምረው ከ500 ዓመታት በፊት በ16ኛው ክፍለ ዘመን ስለመሆኑ ድርሳናት ይጠቁማሉ።

ሕጉን በጊዜው ያረቀቁት አባቶች 44 ሲሆኑ 44ቱም ከኢሳ ብሄረሰብ ተወክለው የተውጣጡ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በሕጉ መሠረት “ገንዴ” ይባላሉ፡፡

ይህ ሕግ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ አስከአሁን እየተተገበረ ያለ የማኅበረሰቡ ሕያው የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ነው፡፡  ይህ ባሕላዊ ሕግ በሂደት ብዙ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ነው ማህበረሰቡን ሲዳኝ ችግሩንም ሲፈታ የኖረው።

ይህ ሕግ የሚያሳየው ነገር ታዲያ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኢሣ ሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት በዲሞክራሲያዊ መንገድ በራሳቸው በተረቀቀ ባህላዊ ሕግ መሠረት ይተዳደሩ እንደነበር ነው። ባሕላዊ ሕጉ ሃይማኖትንም ሆነ መደበኛውን ሕግ በማይጻረር መልኩ የተዘጋጀ ነው። በማኅበረሰቡ የጋራ ስምምነትና ይሁንታ የጸደቀም ነው።

በሦስቱም ሀገራት (በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ) የሚኖሩ የማኀበረሰቡ አባላት ታዲያ የአስተዳደር ማዕከሉን በኢትዮጵያ ድሬዳዋ ከተማ ባደረገ አንድ መሪ ወይንም “ኡጋዝ” ነው የሚመሩት። ይህ ባህላዊ ሕግ ህዝቦችን ያስተሳሰረ በመሆኑ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና አንድነት ሚናው ትልቅ ነው ።

ሕጉ በሦስቱም ሀገራት በሚኖሩ የማኅበረሰቡ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው እኩል የሚተዳደሩበትና የሚጠበቅ ነው።

ታዲያ ይህ ሕግ የወጣውና ተፈፃሚ የሚሆነው ለማንና መቼ ነው?

እርስ በርስ በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ በደሎችንና ከቀላል እስከ ከባድ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ብሎም ሁሉንም እኩል የሚያስተዳድር ሕግ መደንገግ አስፈላጊነቱ በማኅበረሰቡ አባላት በመታመኑና ስምምነት ላይ በመደረሱ ባሕላዊ ሕጉን ለማውጣት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

እነዚህ የኢሳ ህዝቦች አሁን በኢትዮጵያ በጅቡቲ እና በሶማሌ ቢገኙም ሕጉ ተረቋል በተባለበት በ16ተኛው ክፍለ ዘመን ያሉበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተያያዥነት የነበረው ነው። ይህ ባሕላዊ ሕግ የራሱ የሕግ የመተግበሪያ ቦታ ወይንም ሥፍራም አለው፡፡

ከከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች እንደ ፍርድ ቤት የሚገለገሉባቸው የዛፍ ጥላዎችና ወንዞች (በተለይ የደም ካሳ ለመፈጸም የሚገለገሉባቸው የወንዝ ዳርቻዎች) ዋነኛ የመተግበሪያ ቦታዎች ናቸው፡፡

በከተሞች አካባቢ ደግሞ “ጌድካ ነበዳ” ወይም “የሰላም ዛፍ” የተሰኙ ዘመናዊ አዳራሾች በቅርሱ መተግበሪያ ሥፍራነት ያገለግላሉ፡፡

በሕጉ  የተለዩ ችግሮችና ወንጀሎች ሲከሰቱ እንደጥፋቱ ቅለትና ክብደት በሕጉ የተቀመጡ የቅጣት ደረጃዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ። ለምሳሌ በኢሳ ሶማሌ ማኅበረሰብ በማንኛውም ሁኔታ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት የለበትም የሚል ጽኑ እምነት አለ።

ታዲያ ይህንን ዘንግቶ የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ በባሕሉ መሠረት የሚዳኝበትና ሰላም የሚወርድበት የእርቅ ሥርዓት በህጉ ተዘርግቷል፡፡

ለዚህም ማሳያ የሰው ሕይወት ያጠፋ እስከ 100 ግመሎች የሚደርስ በካሳ በመክፈል የተበዳይ ቤተሰቦችን ይክሳል ማለት ነው ። ይህ ሲሆን ግን ካሳውን የሚከፍለው ገዳዩ ብቻ ሳይሆን የገዳዩ ጎሳ በሙሉ ነው።

ሕጉ ሲፈፀም ሰው የገደለ ተብሎ በደፈናው ሳይሆን በቂም በቀል እና በአጋጣሚ የሰው ሕይወት ያጠፋ ተብሎ በሁለት ተከፍሎ ይዳኛል ቅጣቱም የተለያየ ነው።

የኢሳ ማኅበረሰብ የትም ሀገር ቢኖር አንድ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ያለው አንድ የጋራ ኡጋዝ ወይንም መሪ ስለሆነ። ታዲያ ይህ መሪ ወይም ኡጋዙ  በየአካባቢው እንደ መንፈሳዊ አባት ይቆጠራል። ባሕላዊ ሕጉ ፍትሐዊ ሲሆን ለዚህም ማሳያ የመሪው ወይም የኡጋዙ ሥልጣን በዘር የሚተላለፍ አይደለም፡፡

ማንም ሰው ተነስቶም ኡጋዝ አይሆንም። ኡጋዝ ለመሆንም የራሱ የአመራረጥ ሥርዓትና ሕገ ደንብ በሕጉ ላይ በዝርዝር ተደንግጓል። ኡጋዙ ከማኅበረሰቡ ወጣት ትውልዶች መካከል ተፈልጎ ተመርጦ በፖለቲካዊ መሪነትና በመንፈሳዊ አባትነት ዕውቀቱ ተመዝኖ ወደመንበረ ስልጣን የሚመጣ ነው፡፡

ኡጋዙን ለመምረጥ ራሱን የቻለ ዝርዝር ሕግና ደንብ ተቀምጦለታል። የኡጋዙ የሥልጣን ጊዜ የዕድሜ ልክ ነው፡፡ ይሁንና ኡጋዙ በስልጣን ቆይታው የተመረጠበትን ዓላማ ማሳካት ካልቻለ ወይም ሥልጣኑን አላግባብ ከተጠቀመ የመረጠው ማኅበረሰብ እንዳስቀመጠው ሁሉ ሊያወርደው ይችላል።

የኢሳ ሶማሌ ባሕላዊ ሕግ (ሄር ኢሴ) ልክ እንደዘመናዊ ሕግ ሁሉ በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች የተደነገገ እና የተቀመጠ ነው። እነሱም፦

ሄር ዲግ፦ የነፍስ ግድያ ወይም የአካል ጉዳት የሚዳኝበት

ሄር ደቃን፦ ባሕል እና ወግ የሚጠበቅበት

ሄር ደቀቃል፦ የንብረት ጉዳይ ዳኝነት የሚሰጥበት

ሄር ዴር፦ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይኖር የሚከላከሉበት

ሄር ዱል፦ የመሬት ጉዳዮችን የሚያዩበት

ሄር  ዲብለህ፦ ከማህበረሰቡ ውጪ የሆኑ ተበዳዮች ጉዳይ የሚታይበት ሲሆኑ ስድስቱ ዋና ዋና ክፍሎችም 160 አንቀጾች 336 ንዑስ አንቀጾች እና 444 መመሪያዎች አሉዋቸው።

የኢሳ ባህላዊ ህግ የሆነው ሔር-ኢሴ ግን በጥቅሉ ሲታይ ሁለት መሰረታዊ ክፍሎች አሉት እነሱም  "ገንዴ እና ጉዲ" የተባሉት የአስተዳደር መዋቅሮች እና የኡጋዙ ሀላፊነት የተወሰነበት ክፍል ነው። (በዚህ ዘመን አደረጃጀት "ገንዴ" ምክርቤት "ጉዲ" ደግሞ ስራ አስፈፃሚ ልንለው እንችላለን።

ሁለተኛው የህጉ ክፍል ደግሞ የኢሳ ማህበረሰብ እርስበርስ እና ከሌሎች ህዝቦች ጋር የሚኖረውን ግንኝነት በሚመለከት የተደነገገበት ክፍል ነው፡፡

ከተጀመረበት አንስቶ እስከዛሬ "ሔር ኢሴ" የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴና የኑሮ መስተጋብር ሰላማዊ እንዲሆን አድርጓል። በቀጠናውና በድንበር አካባቢዎች የሚከሰቱ ከቀላል እስከ ከባድ ችግሮች ስር ሳይሰዱ በፍትኃዊነት እየዳኘና እርቀ ሰላም እያወረደ ማኅበረሰቡ በሰላም እንዲኖርም ቁልፍ ነው።

"በሔር ኢሴ" ባህላዊ ህግ አለም ለሴቶች ከሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ህጉ ለሴቶች ከፍተኛ ትኩረትና ክብር ይሰጣል። ይህ ሲሆን ግን በዳኝነት ሥርዓት ላይ ሴቶች ተሳታፊ አይሆኑም። ህጉ በሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶችና ወንጀሎች ከፍተኛ ቅጣት አስቀምጧል፡፡

ለአብነትም ልጃገረድ ወይንም ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ሴትን የደፈረ ግለሰብ በባህላዊ ህጉ መሠረት 16 ሴት ግመሎችን ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም ግለሰቡ ከማኅበረሰቡ የተገለለ እና ሌላ ሴት እንዳያገባ ይከለከላል፡፡ ለዚህ ግለሰብ ሴት ልጁን የዳረ ሰውም 12 ግመሎች እንደሚቀጣ ህጉ አስቀምጧል፡፡ ይህ ህጉ ለሴቶች ምን ያህል ቦታና ከለላ እንደሚሰጥ ማሳያ ነው።

ህጉ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን የህጻናት ደህንነትን ከማስጠበቅና ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ ከመከላከል አኳያ የተለያዩ ሕጎች የተደነገጉበት ነው። ሴት ልጅ ትንሽም ትሁን ትልቅ አትገደልም፤ ህጻናትም ራሳቸውን መከላከል ስለማይችሉ አይገደሉም'' ሲል ይደነግጋል።

ዛሬ ላይ በኢሳ ጎሳዎች በተለይም በገጠሩ ክፍል ህጉ ዋነኛ መተዳደርያ ሲሆን በከተማም ቢሆን ከመደበኛው ህግ ጎን ለጎን በአብዛኛው ይተገበራል።

በ16ተኛው ክፍለ ዘመን እንደተረቀቀ የሚነገርለት ይህ ህግ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቀላሉ ሳይረሳ እንዲተላለፍ የረዳው እያንዳንዱ አንቀጽ ሲደነገግ በአባባል መልክ በመቀመጡ ስለመሆኑ ይነገራል።

ዲሞክራሲን፣ ፍትሐዊነትን፣ ሰላምንና የሰውን ልጅ መብት ጠንቅቆ በውስጡ የያዘው የኢሳዎች ባህላዊ ህግ "ሔር ኢሴ" ከህግነት ባለፈ የሶስት ሀገራት ዜጎችን በአንድ ገመድ ያስተሳሰረ ነው።

ዛሬ ላይ ሕጉ በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርሰ ሆኖ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል።

በናርዶስ አዳነ

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top