የፕሪቶሪያው ስምምነት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚለውን ጽኑ አቋሟን በተግባር የገለጠ ነው - ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

2 Hrs Ago 29
የፕሪቶሪያው ስምምነት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚለውን ጽኑ አቋሟን በተግባር የገለጠ ነው - ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚለውን ጽኑ አቋሟን በተግባር የገለጠ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፈረንስ "የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይገባል የሚል ጽኑ አቋም አላት።

በአፍሪካ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሰላም ስምምነቱ ባለፈ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በቀጣናው ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ገንቢ ሚና ተወጥታለች ብለዋል።

ለአፍሪካ ሰላምና ብልፅግና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገቢራዊ መሆን ድርሻው የጎላ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ሴቶችና ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታትና ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶችና አመለካከቶች የሚንጸባረቁባት አይነተ ብዙ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የወል ትርክት ተገንብቶ ህብረ ብሔራዊነት እንዲሰፍን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨትና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በስምምነቱ መሰረት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የሽግግር ፍትህ፣ ብሔራዊ ምክክርና የብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top