በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ በተደረገ ጥናት በርካታ የተሽከርካሪ ዕቃዎች ከ5 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
የጎማ ቁጠባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በክ/ከተማው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ ተከታታይነት ያለው የወንጀለኞች ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
በዚህም ፖሊሲ ህጋዊ የመበርበሪያ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት በማውጣት በጥናት ላይ በተመሰረተ ክትትል በሁለት መኖሪያ ቤት ውስጥና በአንድ ሱቅ ውስጥ ባደረገው ፍተሻ በአዲስ አበባ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሠረቁ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን ከሌቦች እየገዙ በማስቀመጥ መልሰው ለህብረተሰቡ ለመሸጥ የተከማቹ በርካታ የተሽከርካሪ ዕቃዎች ከ5 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።
በተደረገው ፍተሻ 48 የተለያዩ የተሽከርካሪ ስፖኪዮዎች፣ 8 የተሽከርካሪ ሴንተራል ሎክ፣ 6 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጀር ክዳንና ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ ዕቃዎች የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ካከማቹ ግለሰቦች ተይዞ ምርመራው መቀጠሉን ፖሊስ ጠቁሟል።
በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ተፈፅሞብኛል የሚል ግለሰብ ልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በአካል በመቅረብ መረጃ መስጠት እንደሚችልም ተገልጿል።
በተለያዩ ጊዚያት በተለያዩ ክ/ከተሞች የተሠረቀ ንብረት በሚገዙና በሚያከማቹ ግለሰቦች ላይ በህግ አግባብ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በርካቶች ተጠያቂ መደረጋቸውንና ይህም ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡