የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ ነው

22 Days Ago 305
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ ነው

በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ያለ አግባብ ስራ ላይ በመዋላቸው መድኃኒቶቹ ከተህዋስያን ጋር በቀላሉ እንዲላመዱ እንደሚያስችላቸው ይገለፃል፡፡

በዚህም በየዓመቱ በጸረ ተህዋስያን መድኃኒት መላመድ ምክንያት በዓለማችን ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2019 በኢትዮጵያ በገለልተኛ አካላት በተሰራ አንድ ጥናት ከ52 ሺህ በላይ ሰዎች መድኃኒቶችን አላግባብ በመጠቀማቸው ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡

በፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ምክንያት ብዙ ዋጋ ተከፍሎባቸውና ዓመታትን ወስደው የተገኙ መድሃኒቶችን ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ሲሆን በሽታውንም ለማከም አስቸጋሪ እንደሚያደርግ ይገለፃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እንደአብነት ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒና ሲ ሴክሽን እንዲሁም ሌሎች የህክምና ሂደቶችን የበለጠ አደጋ ውስጥ የሚጥል እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ ስለመድኃኒቶቹ አጠቃቀም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ ወጥ የሆነ ጠንከራ ክትትልና ቁጥጥር ያለ መኖር በዋናነት የሚነሱ ችግሮች ሲሆኑ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን ሁሉን አቀፍ ተግባራዊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ይነገራል፡፡

የጸረ ተህዋስያን መድኃኒት መላመድን ለመቀነስ ማህበረሰቡን በሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሞ ማስተማር፣ ማሳወቅና ማስገንዘብ አስፈላጊ ስለመሆኑም ይጠቀሳል፡፡

በምግብና መድኃኒትና ቁጥጥር ባለስልጣን የመድኃኒት መረጃና አጠቃቀም ዴስክ አስተባባሪ አቶ ኃይለማሪያም እሸቴ፤ በጸረ ተህዋስያን መድኃኒት አጠቃቀም ዙሪያ ማህበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ መድኃኒቶችን አላግባብ የመጠቀም ሁኔታ እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከመድኃኒት አቅርቦት ባሻገር የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ኃላፊው፤ የችግሩን መጠን ለመቀነስ እንዲያስችል መድኃኒት አቅራቢዎች፣ ተጠቃሚዎችና አምራቾች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

መድኃኒቶች ማዳን የማይችሉበት ደረጃ ቢደርሱ ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት ቀላል መሆኑን አንስተው፤ ሰው በየትኛውም መድኃኒት አጠቃቀም ዙሪያ የሀኪሙ የምርመራ ውጤትና ትእዛዝ፣ በቂ የፋርማሲ ባለሙያ ውሳኔ ሳይሰጥበት መጠቀሙ ተገቢ አለመሆኑን ይመክራሉ፡፡

ከህዳር 9 እስከ 15 የጸረ ተህዋስያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት እናስተምር፣ እናሳውቅ፣ አሁን እንተግብር በሚል ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡

በመሃመድ ፊጣሞ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top