የሰው ልጅ የሚኮራባቸው አስደናቂ ሥራዎችን እንደመስራቱ የሚጠፋበትን ጉዳይ እንዴት ችላ አለው?

2 Days Ago 797
የሰው ልጅ የሚኮራባቸው አስደናቂ ሥራዎችን እንደመስራቱ የሚጠፋበትን ጉዳይ እንዴት ችላ አለው?

እየተጠናቀቀ ያለው የአውሮፓውያኑ 2024 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደትንግርት የሚቆጠሩ አስደናቂ ሳይንሳዊ ግኝቶች የታዩበት ስለመሆኑ ብዙ አስረጅ አያስፈልገውም። በዚህ የምርምር ዘርፍ ለቀድሞው በብዙ ሃያላን ሀገራት ጥምረት ብቻ ይሞከር የነበረው የጨረቃ ጉዞ አንድ ግለሰብ ወደ ህዋ ለሽርሽር የሚጓዝበት እስከመሆን ደርሷል።

ይህም ብቻ አይደለም በሰው ልጅ የህክምና ጥበብ ውስጥ የሚደረገው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከሰው ወደ ሰው ብቻ የነበረ ቢሆንም ከአሳማ ኩላሊት ወስዶ የጅን አርትኦት በመስራት የአሳማ ኩላሊትን ለሰው በመተካት ስኬታማ የንቅለ ተከላ ሥራ የተሰራበት አመትም ነው።

የሰው ልጅ በምድር ላይ ህይወቱ ኑሮውን ለማቅለል የሚያስችሉትን ቴክኖሎጂዎች በመፍጠር እና መጪው ዘመን አጓጊ እንዲሆን በማድረግ በኩል እስከ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተሰሩት ሥራዎች ቀጥሎ ምርምሩ ምድርን ለቆ ይሄድ ይሆን የሚያስብል እየሆነ ነው።

ይሁን እንጂ እየጠናቀቀ ያለው 2024 የዓለም ሙቀት መጠን ከ1.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ በመጨመር ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዓመት እንደሆነ የሚያመላክተው የኒው ሳይንቲስት ሪፖርት እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ የዓለም ፈተናዎችን ለማለፍ በጎ ዕቅዶች እና መልካም ነገሮችን ከመመኘት ያላልፈ መሆኑ ሌላ አጣብቂኝ ነው።

የህክምና ባልሞያዎች እንደሚሉት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደአስም፣ ብሮንካይተስ፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ሥር የሰደደ የሳምባ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ ናቸው፡፡  

የሰው ልጅ በምድር ላይ እያሳየ ያለውን አስደማሚ ሥራዎች ለተመለከተ ብዙ ተስፋ ቢሰንቅም በአንጻሩ ደግሞ ይሄው የሰው ልጅ መኖሪያው የሆነችው ምድርን ወደሲኦልነት እየቀየራት መሆኑ ለተገነዘበ መጪው ጊዜ አስፈሪ መሆኑን ሊያውቅ ይችላል።

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምትወስነው ውሳኔ ተስፋ የሚሰጡ ደግሞ ለተግባራዊነቱ የሚታየው መጓተት እና ችላ ባይነት ተስፋ የሚያሳጡ ናቸው።

ብዙ ጊዜ የተገባው ቃል አልተፈጸመም በሚባልለት የፓሪስ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የሙቀት መጨመርን በቅድመ-ኢንዱስትሪ ወደነበረበት ለመመለስ ዓመታዊ የሙቀት መጠንን ከ1.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ እንዳያልፍ ለመገደብ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የተገባውን ቃል ለመፈጸም ባለኢንዱስትሪዎች የበለጸጉት ሀገራት ዳተኛ በመሆናቸው የዓለም ሙቀት መጨመር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ይገለጻል፡፡

ለኒው ሳይንቲስት የሚጽፈው ግራሃም ሉተን እንደሚለው በ2024 የአየር ንብረት ለወጡን የሚያባብሱ ምክንያቶች እየጨመሩ መምጣታቸው ቀይ መብራት ሲሆን፣ ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ግን አናሳ መሆናቸውን አንስቷል፡፡

በዚህም ምክንያት ቀጣዮቹ 2025 የፈረንጆች ዓመት አማካይ የሙቀት መጠን በ2023 እና 2024 መካከል ከነበረው የበለጠ በመሆን በታሪክ ከፍተኛው የሙቀት መጠን ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በአውሮፓውያኑ 2035 ዓለም ላይ ከፍተኛ አደጋ ስለሚደቅኑ እና የኩባንያዎች ትርፍ በእጅጉ ስለሚያሽቆለቁል ኩባንያዎቹ በትኩረት ሊሠሩበት እንደሚገባ ደግሞ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም አሳስቧል፡፡

እናም በቀጣይነት የካርቦን ልቀትን ከመቆጣጠር በለፈ ተጨባጭ ተስፋ ላይ እስከሚደርስ ድረስ በቀጣይነት መሥራት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡

የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም የአየር ንብረት ለውጥ እና የኃይል ማመንጫ ሚኒስትር ክሌር ኦኒል ዜሮ የካርቦን ልቀት ላይ ለመድረስ አረንጓዴ ልማት የሚጫወተውን ሚና ይናገራሉ። ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከብክለት ነጻ የሆኑ የኃይል አማራጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል መንግሥታት እና ተቋማት በጉዳዩ ላይ ተናብበው መሥራት አለባቸው ይላሉ ኦኔል፡፡ መንግሥታት እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ደግሞ አረንጓዴ ኢኮኖሚን የሚያበረታቱ ተግባራትን ማበረታታት አለባቸው ነው የሚሉት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምንም በላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ስጋቶችን የቀደመው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሄዱት የአየር ንብረት ጉባኤዎች ላይ የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የገባውን ቃል እንዲፈጽም ለመጠየቅ የቦዘነችበት ወቅት የለም፡፡ ዓለምን አደጋ ላይ እየጣለ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም ሀገራት ዘላቂ መርሐ ግብር ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተሞክሮዎቿን ታጋራለች፡፡ ኢትዮጵያ ባለኢንዱስትሪ ሀገራት ለካርቦን ልቀት ምንም ድርሻ ሳይኖራቸው እየተሰቃዩ ላሉት ታዳጊ ሀገራት ካሳ እንዲከፍሉ ያልጠየቀችበት ወቅትም የለም፡፡ ዓለም የገባውን ቃል እንዲያከብርም በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ቆይታለች አሁንም እየጠየቀች ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሌሎችን ምላሽ በመጠበቅ ላይ ብቻ ተወስና አልቀረችም፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በጀመረችው አረንጓዴ አሻራ የዓለምን ስጋት ለመቀነስ የድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡ በነዚህ ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ከዚህም መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ፀድቋል፡፡ የኢትዮጵያ የደን ሽፋንም በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17.2 ወደ 23.6 አድጓል፡፡ ይህን የደን ሽፋንም በ2022 ዓ.ም ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም አሳሳቢ ችግሮች መፍትሔ የሌላውን የራሷን ድርሻ በተግባር ለመወጣት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡

እንዲህ ያለው መፍትሄ ሁሉም ካልተረባረበበት ለዓለም አይተርፍ የምትለው ኢትዮጵያ ቢያንስ ጎረቤቶቿንም የዚህ መፍትሄ አካል እንዲሆኑ ችግኝ እየሰጠች የዘመቻው አካል ማድረግ ችላለች። ይህ ጉዞ ከጎረቤት ሀገራት አልፎ አፍሪካውያን እና መላው ዓለም እንዲጓዝበት እየወተወተች ነው። 

ከቃል በላይ የሆነ ስጋት እና መደንገጥን የሚጠይቀው ምንድነው?

እንደ ዘ ኒው ሳይንቲስት ዘገባ ዓለም ከቃል ያለፈ ስጋት ውስጥ ካልገባ ለውጥ እንደማይመጣ ያሳያል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በወረቀት ላይ የሚያጓጓ፣ ነገር ግን ተግባራዊነቱ ባዶ የሆነ ቃል ብቻ ዓለምን አያድናትም ይላል ዘገባው። ይልቁንስ እየመጣ ያለውን እና በየአካባቢው እየተከሰተ ህይወትን እየቀጠፈ ያለውን ስጋት ተጋርቶ ሁሉም በፍርሃት መነሳት አለበት ነው የዘገባው አንኳር ሃሳብ፡፡ ዓለም በፓሪስ ተሰብስቦ የዓለም ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ሊሠሩ የሚገባቸውን ዕቅዶች ከዘረዘረ ዘጠኝ ዓመታት አልፈውታል። በየዓመቱም እየተሰበሰበ የፓሪስ ስምምነት ይፈጸም ማለቱንም ቀጥሎበታል፡፡ ይህ ግን ምንም ጠብ ያለ ነገር አላመጣም፡፡ በተለይም በኢንዱስትሪ የበለፀጉት እና ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ሀገራት የገቡትን ቃል ሊፈጽሙ አልቻሉም፡፡ እነዚህ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት እንኳን የገቡትን ቃል ማክበር ቀርቶ ጉዳቱ ባለበት እንዲቆም ሀገራዊ ስትራቴጂ አውጥተው የመሥራት ፖለቲካዊ ውሳኔ አላሳዩም፡፡

ለዚህም ነው "ጉዳዩ ቢወቅጡት እምቦጭ" መሆኑን የተረዳችው ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ አዘጋጅታ ወደ ተግባር የገባችው፡፡ ሌላው ዓለም ግን ዛሬም ምድር በሰደድ እሳት እየተቃጠለች፣ ጎርፍ ከተሞችን እያወደመ፣ ለሰው ልጅ የሚመች ተፈጥሮ እየጠፋ ብሎም ህይወት የሚቀጠፍበት ቅጽበት እየበዛ ሄዶ የየእለት ዜና በሆነበት እንደተኛ ያለ ይመስላል። እናም ዓለምን ወደተፈጥሮዋ መመለስ ወይስ ምድር ሲኦል አድርጎ ሌላ ዓለም መፈለግ የሚለው ምርጫ ለሰው ልጅ የቀረበ ቢመስልም መርጫው ግን አንድ ነው።

 በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top