የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ዩክሬን የሩሲያ ወታደሮች ከያዙት የሀገሪቱ ክፍሎች ማስወጣት እንደማትችል አመኑ።
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ የፈረንሳይ ጋዜጣ ለሆነው ሌ ፓሪስያን በሰጡት ቃለ ምልልስ በሩሲያ የተያዙ ግዛቶችን አሁን ላይ ለማስመለስ ዩክሬን አቅም የላትም ብለዋል።
የቀረው አንድ አማራጭ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ እሱም ዲፕሎማሲ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለሩሲያ አገዛዝ እውቅና ባይሰጡም ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሰራዊታቸውን እንዲያስወጡ ለማድረግ ዲፕሎማሲ ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም ተናግረዋል።
“ግዛታችንን አሳልፈን መስጠት አንችልም የዩክሬን ህገ-መንግስት ይህን እንዳንደርግ ይከለክላል፤ ነገር ግን የሩሲያ ወታደሮች ከያዟቸው ቦታዎች ማስወጣት አንችልም" ብለዋል፡፡
እነዚህ ግዛቶች አሁን በሩሲያውያን ቁጥጥር ስር ናቸው እነሱን ለማስመለስ አቅም የለንም ሲሉም ተደምጠዋል።
አሁን ላይ ፑቲን በድርድር ጠረጴዛ ላይ እንዲቀመጡ ለማስገደድ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ብቻ ነው የምንጠብቀው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ሩስያ በዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል እና በክራይሚያ ብዙ ይዞታዎችን መያዟን የዘገበው ስካይ ኒውስ ነው፡፡
በናርዶስ አዳነ