የምንፈልገው ሰላም እና ልማት ነው የሚል አንድ ድምጽ የተሰማበት ቀን ነው፦ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ

12 Days Ago 191
የምንፈልገው ሰላም እና ልማት ነው የሚል አንድ ድምጽ የተሰማበት ቀን ነው፦ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ
በአማራ ክልል በተካሄዱ ሰልፎች የምንፈልገው ሠላምና ልማት ነው የሚል አንድ ድምፅ የተደመጠበት መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
 
ዛሬ በተካሄዱት ሰልፎች የአማራ ህዝብ ሠላም መፈለጉን ያረጋጠበት እና ችግሮችን በፖለቲካዊና ሕጋዊ መንገድ መፍታት ለሚሹ ሁሉ አቅም የሚሆን ጥሪ ማስተጋባቱን ርዕሠ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ህዝብ በፈቃዱና በሙሉ ቁርጠኝነት በሁሉም ከተሞችና በ266 ወረዳዎች ላካሄደው የድጋፍ ሠልፍም አመስግነዋል።
 
ማህበረሠቡ በሠላም እጦት የከፈለው የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት፣ እገታ እና የኢኮኖሚ ጉስቁልና ይብቃ፤ታጣቂ ቡድኑ ሀገር ከመበጥበጥ እና ከመጠፋፋት አዙሪት ወጥቶ የሠላም አማራጭን እንዲከተል የሚያስታውሱ መልዕክቶች የተላለፉበት ነው ብለዋል።
 
በሀገር ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ማንኛውም ጥያቄ አለኝ የሚል ኃይል በምክክር፣ በሠላማዊና ሕጋዊ መንገድ ብቻ የሚፈታ መሆኑን በማመን የህዝቡ እና የመንግስትን ጥሪ እንዲከተሉም አሳስበዋል።
 
ሠልፉ ለክልሉ መንግስት ልዩ ትርጉም ያለው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መንግስት ያስቀደመውን የሠላም አማራጭ ማህበረሠቡ ቦታ ሠጥቶና ተረድቶ 'ግፍ ይብቃ፤ የሠላም አማራጭን ተቀበሉ' የሚል ጥሪ ቀርቧል ብለዋል።
 
ታጣቂ ኃይሎች ኪሳራና ውድመት ብቻ ትርፉ የሆነ ግጭትን በመተው፣ ማህበረሠቡ ወደፈለገው ሠላም እንዲመጣ ዛሬም በሩ ክፍት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
 
ህብረተሠቡ የሰላም እጦት በቃኝ ብሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሠላም አማራጭን በማይቀበል ላይ መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ ሠላማዊ ሠልፉ የተሳካ እንዲሆን አስተዋጻኦ ላበረከቱ ሁሉም የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
 
በራሄል ፍሬው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top