የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያን የማዕድን ጸጋ በመግለጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ አድርጎታል፡- ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ

3 Days Ago 167
የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያን የማዕድን ጸጋ በመግለጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ አድርጎታል፡- ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ
የለውጡ መንግሥት ተረስቶ የቆየውን የማዕድን ጸጋ በመግለጥ የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ እንዲሆን ማድረጉን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጹ።
 
ሚኒስትሩ በብልፅግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤ የብዝኀ ዘርፍ ኢኮኖሚ የዕድገት ምንጭ የሆነውን የማዕድን ጸጋ መግለጥ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን አውስተዋል።
 
ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ጸጋ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ሆኖም ከለውጡ ዓመታት በፊት ዘርፉ በመንግሥት ዘንድ የተረሳና ለሕገወጥነት የተጋለጠ ነበር ብለዋል።
 
ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፖሊሲና ሕግጋት ጀምሮ የዕይታ ለውጥ በማድረግ የሀገርን የማዕድን ጸጋ የማወቅና የመግለጥ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
 
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድም ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ ትኩረት መስጠቱን አስረድተዋል።
 
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ደግሞ በወርቅ እና በሌሎች ማዕድናት የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።
 
በሌላ በኩል መንግሥት የሲሚንቶ ዋጋና የምርት እጥረት ላይ ህዝቡ የሚያነሳውን ቅሬታ ለመፍታት እርምጃ መውሰዱን በማንሳት የግሉን ዘርፍ በማንቀሳቀስ ግዙፍ ፋብሪካዎች በመክፈት እልባት መስጠቱን ተናግረዋል።
 
በዚህም አሁን ላይ የግንባታ ኢንዱስትሪው ሲሚንቶ በቀላሉ የሚገኝበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያነሱት።
 
በዋናነት በወርቅ ምርት ላይ ብቻ የነበረውን ትኩረት በማስፋት ብዝሃ የማዕድን ሀብት ፍለጋና የማምረት ሂደት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
በዘርፉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ሥራውም በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
 
የሀገር ዕድገት ከማዕድን ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው ያነሱት ሚኒስትሩ፤ማዕድን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ዘርፉ ለህገወጥነት ተጋላጭ በመሆኑ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት አቋቁሞ እርምጃ እየወሰደ ሲሆን፥ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታትም ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ማዕድን ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጠርበትና የዜጎች ህይወት የሚቀየርበት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top