ከተገለበጠ ጀልባ በተዓምር ከተረፈችው ወጣት አንደበት:- አስከፊው ሕገ ወጥ ስደትና መዘ

19 Days Ago 642
ከተገለበጠ ጀልባ በተዓምር ከተረፈችው ወጣት አንደበት:- አስከፊው ሕገ ወጥ ስደትና መዘ

“120 ህገ ወጥ ስደተኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረው ጀልባ ተገለበጠ፤ እኔን ጨምሮ በጀልባው የነበሩ ሰዎች ወደ ባህሩ ሰጠምን፤ በመሃል ውሃው ወደ ላይ አንሳፈፈኝ፤ እዛው የነበረ አንድ ሰው ፈጥኖ ባደረገልኝ ድጋፍ ህይወቴን አተረፈው፤ ... ።” ይህ በሕገ ወጥ መንገድ ለስደት የተዳረገችውና በተዓምር በህይወት የተረፈችው የምህረት ረዘነ ታሪክ ነው። 

በሕገ ወጥ ደላላዎች አማላይ መረጃ ተታለው የተሻለ ሥራ እና ኑሮ ፍለጋ በርካታ ኢትዮጵያውያን የትውልድ ሀገራቸውን ትተው ወደ ባህር ማዶ በሕገ ወጥ መንገድ ይሰደዳሉ። 

በዚህም በዋናነት በሰሜን ምዕራብ ሱዳን ሊቢያን አቋርጠው ወደ አውሮፓ፤ በምስራቅ ወደ ሳውዲ አረቢያ፤ በደቡብ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚወስዱ ዋና ዋና የሕገ ወጥ ስደት በሮችን ይጠቀማሉ። 

በሰው ቤት ተቀጥራ ትሰራበት ከነበረው ውቅሮ ከተማ ኑሮ ከብዷት በጓደኞቿ ግፊት በምስራቅ በር በሕገ ወጥ መንገድ የተሰደደችው ምህረት ረዘነ ሕገ ወጥ ስደት ለሕይወት አደገኛ መሆኑን ትናገራለች። 

ከኢትዮጵያ እስከ ሳውዲ አረቢያ ድረስ ባለው የሕገ ወጥ ስደት ጉዞ መስመር አራት ደላላዎች መኖራቸውን የምትናገረው ምህረት፤ በለስ ቀንቶት የመን መድረስ የቻለ ስደተኛ ቤተሰብ ጋር ደውሎ ገንዘብ ማስላክ ካልቻለ የሚጠብቀው ስቃይ አሊያም ወደ መጣበት መመለሰ መሆኑን ትገልፃለች። 

የበርካቶች ሕልም አረብ ሀገር ደርሶ ሕይወትን መቀየር ቢሆንም፤ በየመን በረሃ በመንገድ ላይ መቅረት፣ በየመንገዱ የሰው አስከሬን እየረገጡ መሄድ፣ ብዙ መከራና ስቃይ ማየት የስደተኞች ዋነኛ እጣ ፈንታ ነው ስትል ታስጠነቅቃለች። 

ዜጎች ወደ የትኛውም ሀገር መሰደድ ሲፈልጉ ሕጋዊ መንገድን መከተላቸው ለሚገጥማቸውን ችግር መፍትሄ ለማግኘትና መብታቸውን ለማስከበር ያስችላቸዋል ትላለች። 

የቤተሰበቿን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በሚል ትምህርቷን አቋርጣ ለ12 ዓመታት በኩዌት በስደት መቆየቷን የምትናገረው ውብእንደእኔ እምቢአለ በበኩሏ፥ የስደት ሕይወትን እንደጠበቀችው ሆኖ እንዳላገኘችው ትናገራለች። 

ሰልጥኖ በህጋዊ መንገድ አለመሄድ፣ ቋንቋ አለመቻል ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍልም ውብእንደእኔ ትገልፃለች። 

በአሰሪዎች መደብደብ፣ ለወራት ያለደመወዝ እንዲሰሩ መገደድ፣ በአካል ላይ ኬሚካል መደፋት፣ ለአእምሮ ጉዳት መዳረግ፣ የአካል ጉዳት ሰለባ መሆን፣ ሳያጠፉ ጥፋተኛ ተብሎ መታሰር የተለመደ መሆኑን ትናገራለች። 

ዜጎች መብታቸው፣ ክብራቸው፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር እንዲሄዱ መንግሥት የሕግ ስርዓት መዘርጋቱን የሚናገሩት ደግሞ በፍትህ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ አቶ እያሱ ቀለሜ ናቸው። 

በ2008 ዓ.ም የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923 በማውጣት እንዲሁም ከመዳረሻ ሀገራት ጋር ስምምነት በማድረግ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከ400-500ሺህ ዜጎች ወደ የተለያዩ ሀገራት መላካቸውን አንስተዋል። 

የሕገ ወጥ ስደት ዋነኛ መንስዔ ለሆኑት ስራ አጥነት፣ የበቂ ክፍያ አለመኖር እና ሌሎች ገፊና ሳቢ ምክንያቶች ምላሽ መስጠት እንደሚገባም አቶ እያሱ አመላክተዋል። 

የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ እፀገነት ኃይሉ በበኩላቸው፥ በተያየዥ ሕጎች ዙሪያ ለፍትህ አካላት ግንዛቤ መስጠት እንዲሁም በመውጫ በሮች ላይ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 

በሕገ ወጥ የሰዎች ንግድ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማትም ካሉ አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ፤ ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲሁም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠጥ እንደሚገባም አሳስበዋል። 

በላሉ ኢታላ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top