በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ኢትዮጵያን ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

1 Day Ago 166
በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ኢትዮጵያን ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ኢትዮጵያን ያገለገሉት እና በበጎ ሥራቸው የሚታወቁት አቶ ሽመልስ አዱኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አቶ ሽመልስ አዱኛ በ1970ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ያስከተለውን ረሃብ ለመቆጣጠር የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በጊዜው የእርዳታ ተግባራትን በማስተባበር አስከፊውን ጉዳት ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ ይበልጥ የሚጠቀሱ ሰው ናቸው።

ከ1977 እስከ 1979 በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አቶ ሽመልስ አዱኛ፤ ከ1979 እስከ 1983 የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስተር ሆነው ሠርተዋል፡፡

ዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይም ስለመሳተፋቸው እና ልዩ ልዩ እውቅናዎችን ስለማግኘታቸው ታሪካቸው ያስረዳል።

አቶ ሽመልስ አዱኛ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በመሆን፣ የኢትዮጵያ የቤተሰብ መምሪያ መሥራች እና የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት በመሆን እንዲሁም በሌሎችም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ኢትዮጵያን አገልግለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ፤ አቶ ሽመልስ አዱኛ በሀገር ባለውለታነታቸውና በበጎ ስራቸው የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

በአቶ ሽመልስ አዱኛ ህልፈተ-ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን የገለፁት ሚኒስትሯ፤ ለወዳጅ ቤተሠቦቻቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top