የአዲስ አበባ የኮሪደርና የመልሶ ማልማት ሰው ተኮር ስራዎች የብልጽግና ፓርቲን ሀገር የመለወጥ ህልም የገለጡ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የመልሶ ግንባታና ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በእንጦጦ፣ ፒያሳ፣ ካዛንቺስ፣ ገላን ጉራና የአቃቂ ቃሊቲ የተቀናጀ የልማት መንደር፣ ለነገዋ የሴቶች የተድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እንዲሁም ብርሀን የዐይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የወንዝ ዳርቻ፣ ኮሪደርና የመልሶ ማልማት ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት በመዲናዋ የተገነቡና በግንባታ ሂደት የሚገኙ ፕሮጀክቶች ትላልቅ ከተሞች ሊያሟሉት የሚገባ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ናቸው።
የመዲናዋ የወንዞች ዳርቻ ልማት እና በእንጦጦ የኮንሶ ወጣቶች የሚያከናውኑትን ገጸ ምድርን የማስዋብ ስራ ጨምሮ አዲስ አበባን ውበት የሚያላብሱ ተግባራት በመሳለጥ ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በፒያሳ አካባቢም ከአንድነትና ወዳጅነት ፓርኮች ጋር ተሰናስለው የሚገነቡ የወንዝ ዳርና የመልሶ ግንባታ ስራዎች የአትሌቲክስ ውድድሮችን ጭምር ማናስተናገድ በሚያስችል መልኩ እየተፋጠኑ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የልማት ሥራዎቹ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን የገቢ አቅም ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ጠቅሰው አብራርተዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ ልማት እና የካዛንችስ ተነሺዎች የሚኖሩበት የገላን ጉራ የተቀናጀ የልማት መንደር ለዜጎች ኑሮ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ተምሳሌታዊ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ነው ሲባልም አቅመ ደካማና ተንከባካቢ ያጡ ዜጎችን የመንከባከብና ህፃናትን የማስተማር ተግባር በማከናወን አንዱ መገለጫ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር፣ የመልሶ ማልማት እና ሰው ተኮር ተግባራት የብልጽግና ፓርቲን ኢትዮጵያን የመለወጥ ህልም የገለጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ሥራዎችን በሁሉም ክልሎች የማስፋት ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፥ በመዲናዋ የሚከናወኑ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳር እና የመልሶ ማልማት የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ከተማዋን የሚያስውቡና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገለጸዋል።
በተለይም የኮሪደር ልማት ስራው የመዲናዋን ዕድገት በማሳለጥ ለዜጎች ዘመናዊ የከተሜነት አኗኗር ዘይቤን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የመንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ ተግባራቱም ለቀጣዩ ትውልድ ምንዳ መሆናቸውን አንስተዋል።
የካዛንችስ የልማት ተነሽ ዜጎች የተሻለ ሕይወት የሚመሩበት የገላን ጉራ የልማት መንደርም በተሰናሰለ የመሰረተ ልማት ግንባታ በጥራትና ፍጥነት የተጠናቀቀ መሆኑን በምልከታ እንዳረጋገጡ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ በመዲናዋ እያከናወነ የሚገኘው የመሰረተ ልማት ግንባታ አዲስ አበባን ጽዱ በማድረግ ለአፍሪካ ምሳሌ የሆነች ከተማ መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
በወንዞች ዳርቻ እየተከናወነ ያለው ልማት ንጹህ አካባቢን ለመገንባት የሚያስችልና ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የመዲናዋ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችም የብልጽግና ፓርቲ መገለጫ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በቀጣይም ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን የሚያላብሱ ውጤታማ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማስፋት ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት በትጋት ይሰራል ብለዋል።
ክልሎች በመዲናዋ በጥራትና ፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እየበቁ ከሚገኙ የልማት ስራዎች ትምህርት በመውሰድ ለዜጎች ተጠቃሚነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፥ በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙ ዘመናዊ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የፈጠሩና አዲስ አበባን በአዲስ ምዕራፍ የሚያስቀምጡ ናቸው ብለዋል።
የልማት ሥራዎቹ አንድ ከተማ የመመስረት ያህል ግዝፈት ያላቸውና የዜጎችን ህይወት በተሰናሰለ አግባብ የሚያዘምኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባን ውብ ገጽታ እያላበሱ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም የብልጽግና ፓርቲን ለሰው ልጆች ቅድሚያ የሰጠ እሳቤ ያነገበ ፓርቲ መሆኑን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።