በዛሬው ኢቢሲ አዲስ ቀን ላይ "በሀገር ጉዳይ" የቀረቡት ማስተር ቺፍ ገረመው ኃይሌ በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ማስተር ቺፍ እንደሚሉት ታዲያ የባሕር ኃይል መፍረስ ከእናት እና አባታቸው ሞት በላይ ያንገበግባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል መፍረስ ዛሬም ድረስ የሚያንገበግባቸው ጉዳዩ የትውልድ ስለሆነ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የባሕር በር ባለቤትነት የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚወስን ነው የሚሉት መኮንኑ፤ ኢትዮጵያ መልሳ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል "ኢትዮጵያ" በተባለችው የመጀመሪያዋ የጦር መርከብ ላይ ለስድስት ዓመታት የሠሩት ፒቲ ኦፊሰር ወንድወሰን አሰፋ በበኩላቸው፤ የባሕር ላይ ሥራ የሴት ልጅን ምጥ ይመስላል ይላሉ፡፡ እናት ልጇ ሲወለድ የምጡን ስቃይ ሁሉ እንደምትረሳው ባሕረኛም ማዕበሎች እና ብዙ የባሕር ላይ ፈተናዎችን አልፎ ወደ ምድር ሲወርድ ያን ሁሉ ስቃይ ይረሳና ሥራውን ይቀጥላል ይላሉ፡፡
ይህን መከራ የሚያስረሳው የባሕር ላይ ሥራ የሀገር ህልውና ማስጠበቂያ መሆኑን የሚያወሱት ፒቲ ኦፊሰር ወንድወሰን፤ እሳቸውም ቤተሰቦቻቸውን ትተው ሁሉን ነገራቸውን ለባሕር ኃይሉ ሰጥተው መኖራቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ሁለት ልጆቻቸው ሲወለዱ እሳቸው ባሕር ላይ ከማዕበል ጋር ሲታጋሉ እንደነበሩ በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡
2 ሺህ 250 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቀይ ባህር ኮሪደር ሜዲትራኒያ ባሕርን እና ህንድ ውቅያኖስ የሚያገናኝ ቁልፍ የውሃ መስመር ነው፡፡ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የንግድ እንቅስቀሴ ይከናወንበታል። ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ንግድ በየዓመቱ በቀይ ባሕር በኩል ያልፋል፡፡
የንግድ መስመሮቹ በዓለም ላይ ካሉት 10 እጅግ ስትራቴጂካዊ የውሃ መንገዶች ሁለቱን ማለትም በባሕሩ ደቡባዊ መግቢያ የሚገኘውን ባብ ኤል-ማንዳብ እና በሰሜን የግብፅ የሚገኘውን ስዊዝ ካናልን ያቋርጣሉ።
የቀይ ባሕር አካባቢ በዘይት እና በከበሩ ማዕድናትም የበለፀገ ነው። ቀይ ባሕር ከ1 ሺህ 200 በላይ የዓሳ ዝርያዎች ያሉበት ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥም 10 በመቶ ያክሉ በቀይ ባሕር ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የዚህ ባሕር ወሳኝ አካል ነበረች፡፡ በአክሱማውያን ሥርዎ መንግሥት ዘመን ኃያል የነበረችው ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ላይ አዱሊስን ጨምሮ በርካታ ወደቦች ነበሯት፡፡ የባሕር ላይ ደህንነቷን ስትጠብቅ የነበረውም እነዚህን ወደቦች ተጠቅማ ነበረ፡፡
በኦቶማን ቱርክ መስፋፋት እየጠበበ የመጣው ሰፊ የኢትዮጵያ የባሕር በር አፍሪካን በተቀራመተው ቅኝ ግዛት ደግሞ የበለጠ አደጋ ውስጥ ገባ፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ዓይኗን የጣለችው እና የምፅዋ ወደብን በኃይል፣ አሰብን ደግሞ ሩባቲኖ በተባለ ኩባንያ አማካኝነት በግዢ የያዘችው ጣሊያንም ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ ከአንዴም ሁለቴ ኢትዮጵያን ወርራለች፡፡
ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር በመዋሃዷ አካባቢውን የሚጠብቅ የባሕር ኃይል እንደተመሰረተ በዛሬው የኢቢሲ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ ላይ የቀረበው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያም በቀይ ባሕር ላይ 1 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ይዞታ የነበራት ሲሆን፣ ይህ ይዞታዋም በባሕር ኃይሏ ይጠበቅ እንደነበረ ታሪክ ዋቢ ተደርጎ ቀርቧል፡፡
ያ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይልም የቀጣናውን ደህንነት ሲያስጠብቅ የነበረ ኃያል ክንድ እንደነበረም መኮንኖቹ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ያንን ኃያል ክንድ ማጣቷ ተሰሚነቷን እንደቀነሰም በቁጭት ያነሱታል፡፡
በዚሁ በኢቢሲ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" ላይ ቀርበው ስለ ቀይ ባሕር አስተያየት የሰጡት አምባሳደር ግሩም አባይ በበኩላቸው፤ ኃያላን ሀገራት በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ዓይናቸውን የጣሉት የባሕሩን አስፈላጊነት በማመን ነው ይላሉ፡፡
ከ10 በላይ ሀገራት ረጅም ርቀት ተጉዘው የጦር ሰፈራቸውን የመሰረቱበት ቀይ ባሕር ላይ ግን ኢትዮጵያ የበይ ተመልካች እንድትሆንበት ተፈርዶባታል፡፡
ኤርትራ በ1985 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ራሷን የቻለች ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያ በአንዴ ሁለት የባሕር በሮችን ማጣቷ ተሰሚነቷን አብሮ የወሰደ መሆኑን የሚጠቅሱት ደግሞ የ"አሰብ የማን ናት?" ደራሲ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ኃይለማርያም ናቸው።
ፕሮፌሰር ያዕቆብ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዛ እና በቀይ ባሕር ቅርብ ርቀት ላይ ሆና የባሕር በር አልባ መሆኗ ኢ-ፍትሃዊነት ስለሆነ የባሕር በር የማግኘት ህጋዊ መብት እንዳላት በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ሀሳባቸውንም በ1997 ዓ.ም በነበረው የምርጫ ክርክርም አቅርበውታል፡፡ በሌላ በኩል ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ በተደረሰው የአልጀርስ ስምምነት ኢትዮጵያ ዳግመኛ የአሰብ ወደብን ባለቤትነት ጥያቄን የማንሳት ዕድል አግኝታ አለመጠቀሟ እንደሚያስቆጭ ጠቅሰዋል፡፡
በርካታ ሰዎች የኢትዮጵያን የባሕር በር ማጣት በቁጭት እያነሱ የነበረ ቢሆንም፣ በኢሕአዴግ ዘመን የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት እንደመዳፈር ይቆጠር ነበረ፡፡ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችንም "የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች" የሚል ታፔላ ይለጠፍባቸው እንደነበረ ብዙዎች በቁጭት ያነሳሉ፡፡
እውነታው ግን የባሕር በርም ሆነ የቀይ ባሕር ጉዳይ ቁልፍ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ጉዳዩም ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ደህንነት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ማብራሪያም ያስረገጡት ይህንኑ ነበረ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ ከህልውናዋ ጋር ከተሳሰረው ቀይ ባሕር መገለል ለቀጣናው አደጋ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በማንኛውም መንገድ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡
ኢትዮጵያ በማንኛውም መልኩ በኃይል እና የሌላውን ጥቅም በመደፍጠጥ ይህ ጥያቄዋ እንዲመለስ እንደማትሠራ እና ይህን ፍትሃዊ እና የማይናወጥ ጥያቄዋን ለመጠየቅ ግን እንደማታፈገፍግ ተናግረዋል፡፡
ይህን የትውልድ ጥያቄ ዛሬ ያለው ትውልድ ማስመለስ ባይችልም ቀጣይ ትውልድ እንደሚያስመልስ እርግጠኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ መሆኑን ያወሱት የታሪክ ተመራማሪ እና የፖለቲካ ተንታኙ ኢብራሂም ሙሉሸዋ (ዶ/ር) ደግሞ የባሕር በር ጥያቄ በመንግሥት ደረጃ አጀንዳ መሆኑ የሚበረታታ እና የትላንትናውን ስህተት ያረመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዮሐናን ዮካሞ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት ዓለም አቀፍ የባሕር ህግ እንደሚደግፋት ጠቅሰው፣ ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድ ገፍታ በመምጣቷ ጥያቄዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በለሚ ታደሰ