የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ጉዳይ

12 Hrs Ago 93
የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ጉዳይ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትናትናው ዕለት ለ5 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት መስጠቱን አስታውቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ካሳለፈው ጊዜያዊ እግድ ጋር አይጋጭም ወይ የሚል ጥያቄን አስነስቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት እንዳይሰጡ በድጋሚ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በዕግዱ ላይ ከታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በየትኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተሰጠ እና የሚሰጥ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገት ተቀባይነት እንደማይኖረውም ያትታል፡፡

የዕግዱ ምክንያትም ከጥቅምት 4/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረው "የአካዳሚክ ሠራተኞች የደረጃ ዕድገት መመሪያ" በመሻሻል ላይ በመሆኑ እንደሆነ ያነሳል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ፤ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገቱን የሰጠው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ''ስለ ራስገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመደንገግ በወጣው'' አዋጅ ቁጥር 1294/2015 መሠረት መሆኑን ይገልጻል፡፡  

EBC DOTSTREAM ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ በመሆኑ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ መሰረት ዕድገቱን የመስጠት መብት እንዳለው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምላሽ አግኝቷል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top