"የወደፊቷ የኢትዮጵያ ተስፋ የብልጽግና እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው" - ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

5 Hrs Ago 45
"የወደፊቷ የኢትዮጵያ ተስፋ የብልጽግና እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው" - ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

የወደፊቷ የኢትዮጵያ ተስፋ የብልጽግናና የሰላም እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለፁ፡፡

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የነበራቸውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ ጉብኝቱን አስመልክቶ በኤክስ ገፃቸው በአማርኛ ቋንቋ ባጋሩት መልእክት፤ ኢትዮጵያ ለሰው ልጅ መገኛነት የመጀመሪያ አሻራ ያላት ሃገር ናት ብለዋል::  

በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በታሪክ ሂደትና በትላልቅ የጋራ ፕሮጀክቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልፀዋል።

እ.ኤ.አ. በ 2019 መሰረታዊ የሆኑ የባህልና የቅርስ ጥበቃን ከሳይንሳዊ ፕሮግራም ጋራ አያይዘን ለመስራት ወስነን ተነስተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በላሊበላ የሰራነው በዓለም ላይ ልዩ የሆነ የቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል ብለዋል።

በአንድ ወቅትም የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት ፕሮጀክትንም ሰርተን ዛሬ የሚያኮራ እውነታ ሆኖ እየታየ ነው ሲሉም አክለዋል።

ወደፊትም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዘመንን ለመደገፍ እና በትግራይ የሰላምና የመረጋጋት መሰረት የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

 

"የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወደፊቷ የኢትዮጵያ ተስፋ የብልጽግናና የሰላም እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው" ሲሉም ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top