ኢትዮጵያ 38ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ በብቃት ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
ለጉባኤው ወደ መዲናዋ የሚመጡ መሪዎችንና ቀዳማዊት እመቤቶችን ለሚያስተናግዱ ዲፕሎማቶችና በጎ ፍቃደኛ የመሪ ባልደረባ ፕሮቶኮሎች ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።
አምባሳደር ብርቱካን ስልጠናውንና የጉባኤውን ዝግጅት በተመለከተ አንዳሉት፣ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በልዩ ትኩረት ቀደም ብሎ ነው የተጀመረው።
ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋን አንስተዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሪዎችና የቀዳማዊት እመቤቶች አስተናጋጅ ጀምሮ በዲፕሎማሲው መስክ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ወጣቶች ተለይተው ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ እንግዶችን በብቃት ለማስተናገድ በተለይም አረብኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋን አቀላጥፈው የሚናገሩ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እንዲሳተፉ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነትን ለማጠናከር እያንዳንዱ ዜጋ በአምባሳደርነት እንዲሰራ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዘንድሮ የመሪዎች ጉባኤ የኮሚሽነሮች ምርጫ የሚካሄድበት እንደመሆኑ በርካታ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ በጎ ፍቃደኛ ፕሮቶኮልና የመሪ ባልደረቦች በበኩላቸው፤ እንግዶችን በክብር በማስተናገድ የኢትዮጵያን እሴት፣ ባህልና የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚያስተዋውቁ ገልጸዋል።
ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አስር ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም፣ 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ ቀደም ብሎ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።