የጉግል አቅጣጫ ጠቋሚ መተግበሪያን በመጠቀም በጎርፍ የፈረሰን ድልድይ ሲሻገሩ ለሞት የተዳረጉት ህንዳውያን

14 Days Ago 204
የጉግል አቅጣጫ ጠቋሚ መተግበሪያን በመጠቀም በጎርፍ የፈረሰን ድልድይ ሲሻገሩ ለሞት የተዳረጉት ህንዳውያን
በህንድ 3 ሰዎች የጉግል አቅጣጫ ጠቋሚ መተግበሪያን በመጠቀም ያደረጉት ጉዞ ለሞት እንደዳረጋቸው ተገልጿል።
 
መተግበሪያው በጎርፍ የፈረሰን ድልድይ እንዲሻገሩ በማመላከት በአካባቢው ባለ ወንዝ ውስጥ ገብተው ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
 
ድልድዩ በጎርፍ አደጋ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ ጥቅም እንደማይሰጥ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ቢያውቁም፤ በአቅራቢያው ይህን የሚገልፅ ምንም ዓይነት የትራፊክ ምልክት እንዳልተቀመጠ ታውቋል።
 
በዚህም የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ብልሽቱን ለጉግል ሊያሳውቅ ይገባ ነበር የሚሉ ትችቶች ተሰንዝረዋል።
 
መተግበሪያው ከካርታ ቀያሽ፣ ከሳተላይት ምስል እንዲሁም ከመንግሥት የሚደርሱትን መረጃዎች በመጠቀም በመንገዶች ላይ የተደረጉ ለውጦች ሲኖሩ መረጃውን እንደሚያዘምን ተገልጿል።
 
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚደርስ አደጋ የመተግበሪያው ባለቤት ተጠያቂ ሊሆን እንደማይገባውና የመንገዱን ደህንነት በተመለከተ አሽከርካሪው በራሱ ግምገማ ሊወስድ እንደሚገባው የኩባንያው ተወካይ መግለፃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
 
በህንድ ታዋቂ የሆነው ይህ የጉግል መተግበሪያ 60 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በቀን 50 ሚሊዮን የሚሆኑ የአቅጣጫ ጥያቄዎችን ያስተናግዳል።
 
ሆኖም ግን መተግበሪያውን በመጠቀም የሚደርሱ አደጋዎች በጊዜ ሂደት ተጠቃሚዎች በመተግበሪያው እንዳይተማመኑ እያደረጋቸው መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
 
በአፎምያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top