የፊፋ የ2024 ምርጥ እግር ኳስ ሽልማት አሸናፊዎች በዛሬው ዕለት በኳታር ዶሃ ከተማ በተካሄደ ስነ ስርዓት ይፋ ሆነዋል።
በዚሁ መሰረት፤ ለሪያል ማድሪድ ክለብ የሚጫወተው ብራዜላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ቪኒሺየስ ጁኒየር የ2024 የውድድር ዘመን የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ተጫዋች ሆኖ በአብላጫ ድምፅ ተመርጧል።
የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ደግሞ የ2024 የውድድር ዘመን የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ወንድ አሰልጣኝ ሽልማትን አሸንፈዋል።
በሌላ በኩል የማንቺስትር ዩናይትድ ተጫዋች አልሃንድሮ ጋርናቾ በኤቨርተን ላይ በመቀስ ምት ባስቆጠራት ግብ የዓመቱ ምርጥ ጎል ሽልማትን ሲያሸንፍ፣ የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ኤሚ ማርቲኔዝ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል፡፡
በሴቶች ደግሞ ለባርሰሎና የምትጫወተው ስፔናዊቷ የእግር ኳስ ኮከብ አይታና ቦንማቲ የ2024 የውድድር ዘመን የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች ሽልማትን አሸንፋለች።
የፊፋ የዓመቱን ምርጥ ደጋፊ ሽልማት የ8 ዓመቱ ታዳጊ ጉሄርሜ ጋንድራ ሞራ ሲያሸንፍ፤ ብራዜላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ቲያጎ ማያ የዓመቱ የፊፋ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማትን ወስዷል፡፡