አዲሱ የኢትዮጵያ የዕድትና የመዘመን ጉዞ ከዘላቂ ልማትና ከጥራት ጋር የተቆራኘ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።
11ኛው ሀገር አቀፍ የተቋማት የጥራት ሽልማት የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት በታላቁ ቤተ-መንግስት ተካሂዷል።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ብቁ የሆኑ የምርትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችም የጥራት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አፅቀ ሥላሴ፤ ጥራት የመወዳደሪያችን ዋና መስፈርት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለጥራትና ተወዳዳሪነት ትኩረት ሳትሰጥ በመቆየቷ ወደ ኋላ መቅረቷን ገልጸው፤ አዲሱ የኢትዮጵያ የዕድትና የመዘመን ጉዞ ከዘላቂ ልማትና ከጥራት ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።
በዚህ ዘመን ጥራት የዓለም የጂኦ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዋነኛ መወዳደሪያ እየሆነ መምጣቱን መረዳት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በጥራት ያመረቱና አገልግሎት የሰጡ ሀገራት ወደ ከፍታ መድረሳቸውን ጠቅሰው፥ ትኩረት ያልሰጡት ግን ወደ ኋላ መቅረታቸውን አንስተዋል።
የተጠቃሚና የተገልጋይን የግንዛቤ ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዝቅተኛ ጥራት ባለው ምርትና አገልግሎት ገበያውን የሚቀላቀሉ አካላት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የሆነው ለጥራት ያለን ባህልና አስተሳሰብ ደካማ በመሆኑ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ መንግሥት ለጥራት በሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያራምድ የጥራት መንደር መገንባቱን አንስተዋል።
የጥራት መንደሩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሁኔታን በቅጡ የመረዳታችን ዐቢይ ምስክር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ አይነቱ ተቋማዊ ግንባታ ሀገራዊ የጥራት አጀንዳችንን ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዕድገትና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ታዬ በንግግራቸው።
በመሆኑም አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች የሀገርን ህልም ለማሳካት፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና አሸናፊ ለመሆን የጥራት መስፈርቶችን መገንዘብና ማሟላት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተሸላሚዎች በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።
የሽልማቱ መሰረታዊ ዓላማ ጥራት ባህል እንዲሆን እና ይህንንም ማስረጽ እንዲቻል መሆኑን አንስተዋል።
ጥራት ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እያደረገችው ላለው ጉዞ አይነተኛ ግብዓት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በ11ኛው የጥራት ሽልማት መርሀ-ግብር ሆራይዘን አዲስ ጎማ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአንደኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።