ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በተለያዩ መስኮች በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራረሙ።
ስምምነቶቹ የተፈረሙት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የኢትዮ-ታንዛኒያ የጋራ የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ ነው።
በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በአቪዬሽን፣ በሕገ-ወጥ ስደት፣ በእንሥሳት እርባታና ማቀነባበሪያ ዘርፎች በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች ናቸው የተፈረሙት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የተፈረሙት ስምምነቶች የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
ለስምምነቶቹ ተፈፃሚነት ሁለቱ አገራት በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የታንዛንያ የውጭ ጉዳይና የምሥራቅ አፍሪካ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ማሕሙድ ታቢት ኮምቦ በበኩላቸው፤ የሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምንቶቹ በፀጥታ፣ በምጣኔ ኃብት፣ በቱሪዝም እና በመሰል ዘርፎች በስፋት መስራት የሚቻልባቸው ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ብልጽግናን እውን ለማድረግ በተያያዘችው ጉዞ በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።