የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ስብሰባው ጠንካራ እና ታሪካዊ መሠረት ያለውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ በፓን አፍሪካ ንቅናቄ ታሪካዊ እና ጉልህ ስፍራ ያላቸው አገራት መሆናቸውን በስብሰባው ላይ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በሁለቱ አገራት በመሪዎች ደረጃ ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ በመግለጽ፤ በቀጣይ በኢኮኖሚ መስኮች ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን እንደ ዕድል በመጠቀም የሁለቱን አገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሁለትዮሽ እና አህጉራዊ የጋራ ፍላጎቶች ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ በግብርና፣ በቱሪዝም እና በሌሎች የትብብር መስኮች ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ሁለቱ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን፣ የህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እና ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ያላቸውን ትብብርም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ሁለቱ አገራት በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች አጠቃቀም በተመለከት ትብብራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።
የታንዛኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ማህሙድ ታቢት በበኩላቸው፤ የመጀመሪያው የሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱ አገራት ስትራቴጂ አጋርነት ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ታንዛንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን ሚኒስትሩ በጋራ ስብሰባው ላይ ገልጸዋል።
በጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ 6 የመግባቢያ ስምምነቶች መፈረማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
ስምምነቶቹ በንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ በአቬሽን፣ በቱሪዝም፣ በግብርና እና በፍልሰትን የተመለከቱ ናቸው።