በሲዳማ ክልል ምስራቅ ሲዳማ ዞን ቦና ዙሪያ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከ 70 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
አደጋው ገላና ወንዝ ድልድይ ላይ ሰዎች አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ የጭነት መኪና መንገድ ስቶ ወደ ወንዝ በመግባቱ እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል።
ተጎጂዎችን የመርዳት እና ሟቾቹን የማፈላለግ ስራ በአከባቢው ማህበረሰብ እና በመንግስት አካላት እየተከናወነ መሆኑ ተጠቅሷል።
ተጎጂዎች በቅርበት ወደ ሚገኘው ቦና አጠቃላይ ሆስፒታል በመወሰድ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
የትራፊክ አደጋ የደረሰበት አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ሰርገኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የአደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑ ተመላክቷል።