"ኢትዮጵያ የአፍሪካ መቀመጫ የሆነችው በአጋጣሚ ሳይሆን ባላት ድንቅ ታሪክ ነው" - የሀገራት አምባሳደሮች

4 Days Ago 186
"ኢትዮጵያ የአፍሪካ መቀመጫ የሆነችው በአጋጣሚ ሳይሆን ባላት ድንቅ ታሪክ ነው" - የሀገራት አምባሳደሮች

የብሔራዊ ቤተ መንግስት የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጻኢ ጊዜዋ ጋር አስተሳስሮ የያዘ ድንቅ ስራ መሆኑን ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።

የታደሰው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት መመረቁ ይታወቃል።

የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችም በብሔራዊ ቤተ መንግስት ጉብኝት አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ መንግስት ቤተ መንግስቱ እድሳት ባከናወኑት ስራ በጣም ኮርቻለሁ፤ ቤተመንግስቱ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሀብትም ጭምር ነው ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት ባለሙያዎችን ያቀፈ የሳይንስ ኮሚቴ በማቋቋም የእድሳት ንድፈ ሀሳብ ማዘጋጀታቸውንና ስራው ከፍተኛ ጉልበት እንደፈሰሰበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የታሪክ ማዕከል የሆነውን ቤተ መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ ብጎበኝም ሁሌም ሳየው አዲስ ይሆንብኛል በማለት መደነቃቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ትልቅ የህይወታቸው ተሞክሮ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቤተ መንግስቱ አሁን ያለው ትውልድ ያለፈውን ታሪኩን መለስ ብሎ እንዲመለከትና ከየት እንደመጣ እንዲያስታውስ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርለት ገልጸዋል።

የፈረንሳይ መንግስት በዚህ ታሪካዊ ስራ ላይ በመሳተፉ ትልቅ ኩራት እንደሚሰማው አክለዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፤ በቤተ መንግስቱ ያደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት በጣም እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ መንግስት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን አስገራሚ ቤተ መንግስት ለማደስ ላወጡት ጊዜ፣ ጉልበት እና ትዕግስት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቤተ መንግስቱ ለረጅም ዘመናት ተደብቀው የቆዩ በርካታ ቅርሶች እና ታሪኮች ዳግም እንዲገለጡ ማድረጉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቷ ያለፈችበትን ስራ በቤተ መንግስቱ እድሳት ማሳየቱን ለመረዳት መቻላቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ታሪክ ለነገ መሰረት ለመጣል ቁልፍ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

የአሜሪካ መንግስት እና ሕዝብም ከባለፈው ታሪኩ በመማር ወደፊት መራመድ የቻለበትን ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ፤ ፈታኝ የነበረው የቤተ መንግስቱ እድሳት ተጠናቆ በመመረቁ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እድሳቱን በጣም ጥሩ ስራ ሲሉ የገለጹት አምባሳደሩ ቤተ መንግስቱ ለቱሪዝም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪኩን እንዲያውቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የታሪክ አካል የሆነውን ቤተ መንግስት ሁሉም በመጎብኘት ሊማርበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ፥ ቤተ መንግስቱ ታድሶ ለሕዝብ ክፍት ከመሆኑ በፊት የመጎብኘት እድል በማግኘታቸው ክብር እንደተሰማቸው እና ባዩት ነገር በጣም እንደተደነቁ ተናግረዋል።

የቤተ መንግስቱ እድሳት ትልቅ ራዕይን በውስጡ የያዘ መሆኑን ገልጸው ራዕዩ የኢትዮጵያን ጉምቱ ታሪክ እና ሀብት ወደ አስገራሚ እውነታ የቀየረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ የአፍሪካ ሕብረትና ከዛም ቀደም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መቀመጫ የሆነችው በአጋጣሚ ሳይሆን ባላት ድንቅ ታሪክ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቤተ መንግስት እድሳት ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን አልፎም የአፍሪካን ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን አገናኝ ድልድይ ነው ብለዋል አምባሳደሯ።

ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በቅርስ ክብካቤና ጥበቃ በትብብር መስራት የሚችሉበት አማራጭ መሆኑን ገልጸው፤ ሀገራቸው በተለያዩ መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትሻ ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top