በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ

2 Days Ago 161
በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ
በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ መንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት ነዋሪዎች ለእንግልትና አላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ለኢቲቪ ገልጸዋል።
 
ነዋሪዎቹ አገልግሎት ፈልገው ወደሄዱባቸው አንዳንድ ተቋማት በቀጠሮ ብዛት እየተመላለሱ ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት መዳረጋቸውን ነው በሰጡት አስተያየት የተናገሩት፡፡
 
ከ8 ወር በፊት የአገልግሎት ክፍያ ባለመፈጸማቸው የውኃ አቅርቦት እንደተቋረጠባቸው የገለጹት አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ፤ ምንም እንኳን የተጠየቁትን ክፍያ ቢፈጽሙም ቆጣሪው መልሶ እንዳልተገጠመላቸው ተናግረዋል።
 
ቅሬታ አቅራቢው በአዲስ አበባ ውኃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮልፌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለ8 ወራት ያህል እየተመላለሱ መሆኑንና እስካሁንም ችግሩ እንዳልተፈታላቸው ነው የገለጹት፡፡
 
ሌላኛው ተገልጋይ ደግሞ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለማግኘት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው በቀጠሯቸው መሰረት መታወቂያቸውን ከኢትዮጵያ ፖስታ በወቅቱ መረከብ አለመቻላቸውን እና ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
 
ለዚህም አሰራሩን በማዘመን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
 
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ተገልጋይ የሆኑት ግለሰብም ለኢቲቪ በሰጡት አስተያየት አገልግሎቱ በአሰራርና በሲስተም የታገዘ ባለመሆኑ ለእንግልት የሚዳርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
በመሆኑም ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ረዥም ሰልፍ ለጠበቅ እና በተደጋጋሚ ወደ ተቋሙ ለመመላለስ እንደተገደዱ ይናገራሉ።
 
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጄንሲ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ዘርግቶ እየተገበረ በመሆኑ፣ ነዋሪዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን አንዳንድ ተገልጋዮች ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡
 
በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ኢቲቪ በአዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" ፕሮግራሙ ላይ ከህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የሰው ሐብት ልማት ስራ ስምሪና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ሰርቪስና ስራና ክህሎት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዩሃንስ መስፍን ጋር ቆይታ አድርጓል።
 
የንዑስ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዮሃንስ መስፍን አገልጋዩ ተገልጋዩን በቅንነትና በተነሳሽነት የማገልገል ግዴታ እንዳለበት በውይይቱ አንስተዋል፡፡
 
ነዋሪዎች በአግልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚያነሱዋቸው አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ትክክለኛ እና አግባብነት ያላቸው ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
 
ዘመናዊ አሰራር ዘርግተው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ፣ ነዋሪውን ለእንግልት የሚዳርጉ መኖራቸውን አንስተዋል።
 
ለዚህም መንግስት የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥትቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአዋጅ የተሰጣቸውን ስልጣን በአግባቡ መወጣት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር የብቃት፣ የጥራትና የፍጥነት ውስንነት እንዳለባቸው በመገንዘብ ምክር ቤቱ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ የማድረግ እንዲሁም የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
 
አዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ ሲደረግ ያጎደሉትን ተጠያቂ የሚያደርግ፣ የተሻለ የፈጸሙትን ደግሞ የሚያበረታታ አሰራር ይኖራል ነው ያሉት፡፡
 
አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ ቀድመው በራሳቸው የጥቆማ፣ የአስተያየትና የቅሬታ አሰራሮችን ዘርግተው ተግባራዊ በማድረግ ላይ ያሉ ተቋማት ስለመኖራቸው አቶ ዮሃንስ አንስተዋል፡፡
 
የአዋጁ መተግበር አሁን ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ይፈታዋል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ዮሃንስ ምላሽ ሰጥተዋል።
 
በምላሻቸውም የአዋጁ መተግበር ብቻውን መፍትሄ አያመጣም ያሉ ሲሆን፣ ብቃትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በምዘና ከፍተኛ እና መካከለኛ በሚል የተለዩ አገልግሎቶች ላይ እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
 
በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top