በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰተ ባለው የርዕደ-መሬት ክስተት ሁኔታና ምላሽን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

2 Days Ago 177
በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰተ ባለው የርዕደ-መሬት ክስተት ሁኔታና ምላሽን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የርዕደ መሬት ከስተት የተፈጥሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደወለን ተከተሎ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በእስካሁኑ ሁኔታና ምላሽ እየታየ ያለው ስራ አመርቂ ነው፡፡

በአፋር ከልል ሁለት ወረዳዎች ማለትም አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ (ዱለሳ) ወረዳዎች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው:: በሁለቱም ወረዳዎች ማለትም በአዋሽ ፈንታሌ 6 ተጋላጭ ቀበሌዎች 15 ሺህ ነዋሪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ እስከ አሁን 7 ሺህ ወገኖች ከስጋቱ ቀጠና ወደ ሌላ ስፈራ ተጓጉዘዋል፡፡

በዱለቻ ወረዳ ደግሞ 20 ሺህ የሚሆኑ የ2 ቀበሌዎች ወገኖች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ቀበሌዎች እስከ አሁን 6 ሺህ 223 ህዝብ አካባቢውን ለቀዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የ5 ቀበሌዎች ወገኖች ለአደጋው ተጋላጅ ናቸው:: በ5ቱም ቀበሌዎች 16 ሺህ 182 ሕዝብ ተጋላጭ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ 7 ሺህ 350 ሕዝብ ከተጋላጨ ስፍራ ወጥተዋል፡፡ 8 ሺህ 832 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ሰዎች ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከስፍራው እንዲንቀሳቀሱ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ክስተቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ የሳይንቲፊክ ኮሚቴ፣ ያለውን ሁኔታ እየተከታተለ ሲሆን መገለጽ ያለበትን ቅድመ-ጥንቃቄዎች አስመልከቶ አስፈላጊው መረጃ ለሕዝብ በተከታታይ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ይህንንም ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማህበራዊ ሚዲያዎችና ድህረ ገጽ መከታተል ይቻላል፡፡

የርዕደ መሬት ንዝረቱ ባለበት አካባቢ ያለ ማህበረሰብ ከንዝረቱ በፊት፣ በንዝረቱ ወቅትና ከንዝረቱ በኋላ ያለውን መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄ እንዲወስዱ አስፈላጊው መረጃ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ እስከ አሁን ለ70 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን 11 ሺህ 550 ኩንታል ምግብ-ነክ እና ለ700 አባወራ የሚሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው ተልኳል፡፡ ይህም በንዘብ ሲተመን ለምግብ ብር 216 ሚሊየን 562 ሺህ ብር በላይ  እና ምግብ ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች 65 ሚሊየን 625 ሺህ ብር  በድምሩ 281 ሚሊየን 562 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ነው፡፡

በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል የርዕደ መሬቱን ባህሪያትና የሚጠይቀውን የጥንቃቄ መልዕከቶች በተከታታይ የምናቀርብ በመሆኑ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ አደጋውን ለመሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በንታት እንዲንቀሳቀሰ እናሳስባለን፡፡

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top