የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ እድሳቱ በተጠናቀቀው የኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት ምርቃት ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቤተ-መንግሥቱን ከፍ ያለ ኪናዊ ጥበብን የተላበሰ ብቻ አድርጎ መውሰድ በቂ አይሆንም ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ ቤተ-መንግሥቱ ተጋድሎአችን፣ አያሌ ፈተናዎቻችን እና ድላችን የሚነበብበት ድርሳን፤ የታሪካችን መድብል ነው ሲሉ ገልፀውታል።
እያንደንዱ መሪ ሀገር ከማስተዳደር እና ከመምራት ባሻገር የራሱ ቅኝት፣ የራሱ ሀሳብ፣ የህይወት መሻት፣ ራዕይ እና ምኞት ይኖረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህን ቤተ-መንግሥት ለመገንባት የነበረው የሀሳብ ፍሰት እና ፍላጎት ግዙፍ እና ውብ የሆነ ቤተ-መንግሥት ከመገንባት ያለፈ መሆኑን አመላክተዋል።
ዘመናዊነትን ለማስተዋወቅ እና የድል ብሥራትን ለማመላከት እንዲሁም አዲስ አበባ ነጻነት ላገኙ የአፍሪካ ሀገራት የነጻነት መቅረዝ እና ዓለም አቀፍ መዲና እንድትሆን ታስቦ የተገነባ ቤተ-መንግሥት መሆኑንም አውስተዋል።
በዚህም ምክንያት ቤተ-መንግሥቱ የኃይል ፍላጻ ማመላከቻ እንዲሆን ታስቦ መሠራቱን እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
በ1942 ዓ.ም ዓለም አቀፍ አርክቴክቶች በንድፉ ውድድር እንዲሳተፉ መደረጉን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ታየ፤ ዕድለኛው አሸናፊ ግን መቀመጫውን ኢትዮጵያ ያደረገው የስዊስ ዜጋ እንደነበረ እና ውድድሩም አዲስ አበባን የመሃንዲሶች እና አርክቴክቶች የስበት ማዕከል እንዳደረጋት ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ቤተ-መንግሥቱን ተከትሎ እንደ ብሔራዊ ቴአትር፣ የአፍሪካ አዳራሽ፣ አዲስ አበባ ስታዲየም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሂልተን አዲስ አበባ ያሉ ህንጻዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በቤተ-መንግሥቱ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት መስተጋብር ጎላ ብሎ እንደሚታይ ጠቅሰው፤ ቦታው ከንጉሠ ነገሥታዊ ውስብስብ ስብሰባዎች እስከ ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች የተለያዩ አሻራዎች የሚታዩበት፤ የአፍሪካ መሪዎች ከቤተ-መንግሥቱ አንስቶ እስከ አፍሪካ አዳራሽ የእግር ጉዞ በማድረግ የአፍሪካን መሻት የመከሩበት እንደሆነ አውስተዋል።
የቤተ-መንግሥቱ አዳራሽ የኢትዮጵያን የፓን አፍሪካኒዝምን መሻት እና የፓን አፍሪካን አቀንቃኝ መሪዎቿን ራዕይ አስማምቶ የአህጉሪቱን ዕጣ ፈንታ መቅረጽ የተቻለበትም ነው ብለዋል።
ከቤተ-መንግሥቱ እስከ አፍሪካ አዳራሽ በነበረው የእግር ጉዞ ወቅት በንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ እና በአፍሪካ ባለራዕይ መሪዎች በተለይም በንጉሠ ነገሥቱ እና በጊኒው ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ መካከል የአባት እና የልጅ ቅኔ መፍሰሱንም ፕሬዚዳንት ታየ አስታውሰዋል።
ይህ በንጉሠ ነገሥቱ እና በአፍሪካ ባለራዕይ መሪዎች መካከል የነበረው የአባት እና ልጅነት መንፈስ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ወቅት የነበረውን የካዛብላንካ እና የሞንሮቪያ ቡድኖችን የልዩነት መጋረጃ የቀደደ እንደነበረ ነው ፕሬዚዳንት ታየ የገለፁት።
በወቅቱ ኢትዮጵያን የጎበኙ በርካታ የዓለም መሪዎች በቤተ-መንግሥቱ በር ማለፋቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንት ታየ፤ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን፣ የቀድሞ የዩጎዝላቪያ መሪ ፕሬዚዳንት ቲቶ፣ የኢራኑ ሻህ ፓህላቪ፣ የግሪኩ ንጉሥ ጳውሎስ እና የዮርዳኖሱ ንጉሥ ሁሴን ቤተ-መንግሥቱን መጎብኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የጃፓኑ ልዑል አኬቶ የጃፓን አትክልት ሥፍራን በቤተ-መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመፍጠር ራሳቸው አትክልተኛ ሆነው ችግኝኞች መትከላቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ፤ ያን አጋጣሚ ማስታወስ ኢትዮጵያ መሪም አትክልተኛም ለማግኘት ብዙ ዓመታት እንደወሰደባት ያስረዳል ብለዋል።
የ1970ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ፈታኝ እንደነበሩ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፤ ቤተ-መንግሥቱ በመደነቅም፣ በመገረምም፣ በሀዘንም በተፈራረቁ ስሜቶች የራሱን ትንሳኤ እና የራሱን ውድቀት እንደታዘበ ጠቅሰዋል።
ደርግ መቀመጫውን ከኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት ወደ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ሲለውጥ በውስጡ ያሉትን ስብስቦች አስጠብቆ መቆየቱን አስታውሰው፤ ለዚህ ደግሞ የቤተ-መንግሥቱን ፋይዳ እና ቀጣይነት ላከበሩት ብርጋዴር ጄነራል ፍሬሰንበት አምዴ እና ታማኝ የቤተ-መንግሥቱ ሲቪል ሠራተኞች የላቀ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በ2007 ዓ.ም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ግቢውን በእግራቸው ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ታየ፤ ከሉሲ ጋር ተዋውቀው የጥቁር አንበሳ ደንን ከጎበኙ በኋላ ወደ ግብር አዳራሹ አምርተው፣ ወደ ዙፋኑም አቅንተው መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህ ቤተ-መንግሥት በሚገባው ልክ ታድሶ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን መወሰናቸው የቤተ-መንግሥቱን ታሪካዊ እና ህያው ፋይዳ ከፍ ብለው ስለመገንዘባቸው ማሳያ እንደሆነም ፕሬዚዳንት ታየ ጠቅሰዋል።
ታሪክ በቤተ-መንግሥት ካዝና ተቆልፎበት የሚቀመጥ ሳይሆን ክፍት ሆኖ የምናየው፣ የምናነበው፣ የምንማርበት እና የምናደንቀው፤ ከዛሬው ፍላጎታችን ጋር አስማምተን የምንጓዝበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የጫካ ፕሮጀክትም ከዚህ ማሰላሰል እና ዘመናዊነትን ከማስቀጠል ሀሳብ የመነጨ እንደሆነ እንደሚሰማቸው እና በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ዛሬ ዳግም የተወለደው ይህ ቤተ-መንግሥትም የቱሪስት መስህብ፣ የባህል ልውውጥ እና የዲፕሎማሲ እንዲሁም የውይይት እና የትብብር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታቸውን ገልጸዋል።
ቤተ-መንግሥቱ መጪው ትውልድ ከቀደሙት ሰዎች ውርስ ጋር የሚገናኝበት የታሪክ ሀብል እና ሰንሰለት እንደሚሆን አውስተው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን ታሪካዊ ሁነት በማሳካታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
የፈረንሳይ መንግሥት በተለይም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበው፤ ይህም ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ያላቸውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው ተናግዋል።