የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ረገድ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል፡- ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

3 Days Ago 189
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ረገድ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል፡- ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ሕገ ወጥና የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
 
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያዘጋጀው ሶስተኛው ብሔራዊ የፀረ- ህገወጥ ንግድ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ የሀገር ኢኮኖሚ ስብራት መንስዔ ሆኖ ቆይቷል።
 
መንግሥት የንግዱን ዘርፍ እየፈተነ ያለውን ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በንግድ ሥርዓቱ ላይ ገቢ ስወራ፣ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ምርት ደብቆ ማቆየት፣ በምርት ላይ ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ ዋጋ መጨመርና ሌሎች ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በተጨማሪም በገቢና ወጪ ንግድ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የመንግሥት እና የህዝብን ሀብት እያባከነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ህጋዊ የንግድ ሥርዓቱን ተከትለው የሚሰሩ በርካታ ታማኝ ነጋዴዎች የመኖራቸውን ያህል በአቋራጭ ለመክበር የሚተጉ ስግብግቦች እንዳሉም አንስተዋል።
 
በመሆኑም መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት አሰራርና ፖሊሲ ዘርግቶ ባከናወነው ተግባር ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
 
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ረገድ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት።
 
በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራን ተከትሎ በህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በተሰማሩ 108 ሺህ ነጋዴዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ህግ ተጠያቂነት የሚደርስ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
 
ሪፎርሙ በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የነበረውን 29 ነጥብ 2 የዋጋ ግሽበት ከ20 በታች ማውረድ መቻሉን ጠቁመዋል።
 
በ2016 በጀት ዓመት ከቁም እንስሳት ወጪ ንግድ ዓመታዊ ገቢ 18 ሚሊየን ዶላር እንደነበር አውስተው፣ ከሪፎርሙ ወዲህ በአምስት ወራት ብቻ 20 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።
 
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በበኩላቸው በቁም እንስሳት፣ በቡናና ፋርማሲዩቲካል ምርቶች ላይ የሚከናወን ሕገ ወጥ ንግድ የሀገርን ኢኮኖሚ እየተፈታተነ ነው ብለዋል።
 
ህገወጥ ንግድ የመንግሥትን ገቢ በመቀነስ የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያቀጭጭ፣ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ የሚያስወጣ የሀገር ልማት ጠንቅ መሆኑንም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በመሆኑም መንግሥት ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ሀገራዊ ልማትን እንዲያከናውን ህገወጥ ንግድን በጋራ ልንከላከል ይገባል ነው ያሉት።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top