ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እየሠራች ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

2 Days Ago 100
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እየሠራች ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፤ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እና ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተመራ ልዑካን ቡድን በጎረቤት አገራት ጉብኝት ማድረጉን ገልጸዋል።

አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቴዎስ የተመራው ልዑክ በቅርቡ በጂቡቲ እና በኬንያ እንዲሁም በመከላከያ ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሀመድ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ ጉብኝት ማድረጉን በመግለጫቸው አንስተዋል።

ቃል አቀባዩ ይህ ተከታታይ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የጎረቤት አገራት ጉብኝት ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር እና ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግ ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እየሠራች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በጉብኝቱም ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

አሸባሪው አልሽባብን በጋራ በመዋጋት የቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት የተረጋገጥ እንዲሆን በሚደረገው ጥረትም የሰሞኑ ጉብኝቶች እና ውይይቶች ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።

አምባሳደር ነብያት በቀጣይ በየካቲት ወር በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የጉባኤው ተሳታፊዎችን በኢትዮጵያዊ ባህል እና ዕሴት ልዩ መስተንግዶ በማድረግ የኮንፈረንስ ገቢን ለማሳደግ እና የገጽታ ግንባታ ለመሥራት ታቅዶ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

በቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ላይ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ሥልጠና በመውሰድ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ዲፕሎማት ነው የሚለውን መርህ ለማሳየት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top