ከሰም ስኳር ፋብሪካ በመሬት መንቀጥቀጡ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱ ተገለፀ

1 Day Ago 215
ከሰም ስኳር ፋብሪካ በመሬት መንቀጥቀጡ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱ ተገለፀ

በአፋር ክልል ዱላሳ ወረዳ የሚገኘው የኢፌዴሪ ከሰም ስኳር ፋብሪካ በመሬት መንቀጥቀጡ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል።

በአፋር ክልል ዱላሳ ወረዳ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ በስኳር ፋብሪካው አስተዳደር ህንፃ፣ በኃይል ማስተላለፊያ ክፍል፣ የላብራቶሪ እና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን የፋብካው ስራ አስኪያጅ አቶ አሊ ሁሴን ኡመር ለኢቲቪ ተናግረዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ በከፍተኛ ሁኔታ በአከባቢው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ጉዳት በደረሰባቸው ህንፃዎች ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ንብረቶችን ለማዳን የመሬት መንቀጥቀጡ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነባቸው ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

የፋብሪካው ሰራተኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድሞ እንዲለቁ መደረጉን የገለፁት አቶ አሊ ሁሴን፤ ከተፈጥሮ አደጋ በተጨማሪ በፋብሪካው ንብረት ላይ ስርቆት እንዳይፈጸም ከመከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና ከዞን ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የፋብሪካውን ንብረት ለማትረፍ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል። 

ከ4 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያለው የከሰም ስኳር ፋብሪካ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ስራ ማቆሙ ተጠቅሷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት የርዕደ መሬቱ ማዕከል ከሆኑ አካባቢዎች ነዋሪዎችን የማራቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስታወቁ ይታወቃል፡፡

በተለይም የርዕደ መሬቱ ማዕከል የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በቦታው በማሰማራት የጉዳቱን መጠን አሰሳ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማስፈር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በሁሴን መሃመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top