8ቱ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ልማዶች ከዓለም ዙሪያ

1 Day Ago 720
8ቱ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ልማዶች ከዓለም ዙሪያ

ቱሪዝም ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው ሎንሊ ፕላኔት የተባለው ድረገጽ “8 የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል አከባበር ልማዶች ከዓለም ዙሪያ” በሚል ርዕስ ስር ባስነበበው ጽሁፉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በገና ሰሞን ለየት ያለ የአከባበር ባሕል ያላቸውን አገራት ልምዶች አካፍሏል።

ኢትዮጵያ የተካተተችበት ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ባህል ምን ይመስላል?

  1. ታኅሣሥ 29 ቀን (በጃንዋሪ 7) የሚከበረው የኢትዮጵያ ገና

“መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታሪክ እንደሚነግረን ሦስት ጠቢባን ለተወለደው ሕጻን እጅ መንሻ ለማቅረብ በኮከብ እየተመሩ ከምስራቅ ወደ ቤተልሄም ሄዱ፡፡” እናም እነዚህ ሦስት ጠቢባን ከእስያ፣ አውሮፓ እና ኢትዮጵያ የሄዱ እንደነበሩም ይነሳል። ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ሦስቱ ጠቢባን (12 ናቸው የሚሉም አሉ) በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለውም ያምናሉ ይላል ድረ-ገጹ በጽሁፉ።

የኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር ከጁሊያን የዘመን ቀመር ጋር የሚስማማ ነው የሚለው የዚህ ድረ ገጽ ዘገባ ይህም በመሆኑ የክርስቶስ ልደትን በታኅሣሥ 29 (January 7) እንዲያከብሩ አስችሏቸዋል ብሏል፡፡ እናም ኢትዮጵያውያን በዓሉን በሚያከብሩበት ጊዜ ነገሥታት የሚያስመስላቸውን ነጭ በነጭ ለብሰው፣ ጥለት ያለበት ነጠላ አጣፍተው፣ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ እንደሚያከብሩት ነው ያተተው፡፡

  1. ያሸበረቁ ቀን መቁጠሪያ የሚሰቅሉት ጀርመኖች

ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ ካሉት አራት እሁዶች ጀምሮ "አድቨንት (Advent)" የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከላቲን የተወሰደ ቃል ሲሆን መዳረሻ የሚል ትርጉም አዝሏል፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በጀርመን የሚገኙ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች 24 መስመሮችን በራቸው ላይ በጠመኔ (ቾክ) በመሳል በቀን አንድ እያጠፉ እስከልደት ያለውን ቀን የመቁጠር ልማድ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በወረቀት የተሰሩ የመዳረሻ ቀን መቁጠሪያዎች በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመሩ ልማዶች ናቸው ፡፡

ግርሃም ላንግ የተባለ ጀርመናዊ እናቱ  በልጅነቱ ትሰራለት በነበረው ቀን መቁጠሪ መነሻነት ለመጀመሪያ ጊዜ በብዛት ያመረታቸው ቀን መቁጠሪዎች የሽያጭ ስኬት አስገኙለት፡፡ ቀጥሎም የሚከፈቱ በሮች ያሉባቸውን ካርዶች መስራት እንደሚቻል ሐሳቡ መጣለት፡፡ አሁን አሁን ይህ የካርድ ሥራ ተስፋፍቶ በትላልቅ መጠን በመሰራት በከተሞች መግቢያ፣ አደባባዮች እና በቤት ፊትለፊት ማድረግ የተዘወተረ ልማድ ሆኗል፡

  1. ጥድ ዛፎችን ማስዋብ በአውሮፓ

አረማዊ አውሮፓውያን በክረምት ወራት ጥዶችን እየቆረጡ ወደ ቤታቸው ያመጡ ነበር፡፡ የዛፍ አምልኮ የተለመደ በመሆኑ በአካባቢያቸው የሚገኙ ዛፎች ላይ ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትን የሚወክሉ ጌጣጌጦች አድርገውባቸው በማስዋብና ሻማ በማብራት ይከናወን  ነበር፡፡

በስካንዲኒቪያን ቤትን እና ግቢን በአረንጓዴ ቅጠሎችና ቀለማት በማስዋብ ርኩስ መናፍስትን ለመከላከል ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ልምላሜ የዘላለማዊ ሕይወት ምሳሌ እንደመሆኑ መጠን በአውሮፓ የፀደይ ወራት መምጣትን ለማብሰር በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላል።

አሁን አሁን በመላው ዓለም የገና ዛፍ ማዘጋጀት የተለመደ ቢሆንም በሰነድ ተመዝግቦ እንደሚገኘው በመጀመሪያ ጥቅም ላይ የዋለው በኢስቶኒያ ተሊን ከተማ  እና በሪጋ ከተማ ላቲቪያ ውስጥ ነበር ፡፡

  1. የትንሿ ሻማ ምሽት

በኅዳር 29 (December 7) የድንግል ማርያምን በንጽሕና መውለድ ለማሰብ ሻማ በማብራት የሚከበር ዕለት ነው፡፡

በኮሎምቢያ በቤታቸውና በጎዳናዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሻማዎችን ያበራሉ፡፡ በየጊዜውም ፈጠራዎች እየታከሉበት የበለጠ እየተስፋፋ የመጣ ልማድ ነው፡፡ 

  1. የፖንሴቴ አበባ ስጦታ በሜክሲኮ

ፖንሴቴ በመካከለኛው አሜሪካ በተለይም በሜክሲኮ በገና ሰሞን የሚያብብ ደማቅ ቀይ አበባ ነው፡፡ በሜክሲኮ አፈታሪክ በክርስቶስ ልደት ዋዜማ አገልግሎት ላይ የነበረች ልጃገረድ ለሕጻኑ ክርስቶስ ማቅረብ የቻለችው ስጦታ ርጥብ ቅጠልን ነበር፡፡ የያዘችውን ቅጠል በርከክ ብላ ስታቀርብ በድንገት ቀይ አበባ አፈነደቀ፡፡ የአበባው ቅርጽም የመሪ ኮከቡን ቅርጽ የያዘ በመሆኑ የተቀደሰው ምሽት አበባ ተብሎ የክርስቶስ ልደት ምልክት ሆነ የሚል ታሪክን መነሻ በማድረግ አሁን ይከበራል፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የሜክሲኮ ሰዎች የፖንሴቴ አበባን የልደት ስጦታ አድርገውት ቀጥለዋል።

  1. ዲያቢሎስን ማቃጠል በጓቲማላ

በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ዋዜማ አመሻሽ ላይ የጓቲማላ ዜጎች በከተሞች እና መንደሮች አደባባይ በመሰብሰብ በዓሉን ያከብሩታል።

በዚህ በዓል ላይ በዲያቢሎስ አምሳል የተሰራ ቅርጽ ሰርተው በማቃጠል ያከብሩታል። ይህ ልማድ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ዓመት ከክፉ መንፈስ እንዲጠበቁ እንደሚያደርግ ያምናሉ፡፡

  1. የሌሊት መርሃ ግብር በሮም

ብዙ የሥነ-መለኮት አጥኚዎች እንደሚያምኑት በሌሊት የመጣው የክርስቶስን መወለድ መሰረት አድርጎ ችቦ በማብራት ወደ እየሩሳሌም ከተደረገ ሃይማኖታዊ ጉዞ ጋር ነው፡፡ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሮም የሄዱ ተጓዦች የልደቱን ዋዜማ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በቤተልሄም በችቦ ማብራት ሌሊቱን አሳለፉ፡፡

በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅድስት ማርያም መንበረ ታቦት (ባሲሊካ ማርያም) ቤተክርስቲያን በሮም ሲገነባ የወቅቱ ጳጳስ (pop sixtus)  በአዋጅ እንዲከበር በማዘዛቸው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሥርዓቱ እየተስፋፋ ቀጥሏል፡፡

  1. የልደት ዋዜማ በኪዩቤክ

በኪዩቤክ በልደት ዋዜማ የሚከበረው ለንጋት አቅራቢያ ነው፡፡ በባህሉ ቤተሰቦች የሌሊት መርሃ ግብርን ከተካፈሉ በኋላ ወደ ቤት ከመድረሳቸው በፊት የገና አባት ስጦታ እንደሚያስቀምጥ ይጠብቃሉ።

ቤታቸውን ከፍተው እንደገቡም የተጠበሰ ስጋ የገባበት ብስኩት ፣ የድንች ገንፎ፣ የተጠበሰ የቱርክ ዶሮ በበሰለ ዛጎል እንዲሁም በኬክና  በሌሎች ጣፋጭ ምግቦች በጠረጴዛቸው ሞልቶ እየተበላና እየተጠጣ ይነጋል።

በተስፋዬ ባዩ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top