የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሰሞነኛ የመሬት መንቀጥቀጥን (ንዝረትን) አስመልክቶ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ይፋ አድርጓል።
የጥንቃቄ እርምጃዎችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ያጋራው ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
የመሬት ንዝረት/መንቀጥቀጥ/ ክስተት ጋር ተያይዞ ከክስተቱ በፊት፣ በክስተቱ ጊዜና ከክስተቱ በኃላ ሊወሰዱ የሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች፤
በየትኛውም ወቅት የመሬት ንዝረት ወይም መንቀጥቀጥ በሚከሰትበት ጊዜ ከሁሉም ነገር በፊት አለመሸበር፣ መረጋጋትና ሊወሰዱ የሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችን በጥንቃቄ ማከናወን፤ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን መከታተልና ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ትክክለኛ ያልሆነና ከትክክለኛ ምንጭ ያልተገኘ መረጃዎችን አለመቀበልና አለማሰራጨት እጅግ ተፈላጊ ባህሪያት ናቸው፤
ማንኛውም ግለሰብና ቤተሰብ የፀጥታና ደህንነት ችግሮች እንዳያጋጥሙ በየአካባቢው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር የመሥራት ኃላፊነት አለበት፡፡ በተጨማሪም በአደጋ ስጋት ምክንያት በተከለሉ አካባቢዎች አለመንቀሳቀስ ተገቢ ሲሆን ከዚህ በታች የተመለከቱት የጥንቃቄ መልዕክቶችም በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው፡፡
- የመሬት ንዝረት ከመከሰቱ በፊት፤
- ከቤቱ ወይም ከህንፃው ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚቻልና የት ላይ መሰብሰብና መቆየት እንዳለብን ማወቅ፤
- በአደጋ ወቅት ከጣራ ወይም ከከፍታ ቦታ ከሚወድቁ ቁሳቁሶች ራስን ለመከላከል የሚያስችሉ መከለያዎችን መጠቀመ (ጠረጴዛ፣ ዴስክ፣ ምሶሶ፣ ወዘተ)፤
- የነዳጅ፣ የጋዝ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች እንዴት ቶሎ እንደሚዘጉ እና እንደሚቋረጥ አስቀድሞ መለማመድ፤
- በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት የሚወድቁና ጉዳት የሚያደርሱ ትላልቅ ዕቃዎችን መለየት፤ አስቀድሞ ማስወገድ፤
- ሊቀጣጠሉ ወይም አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ፈሳሾችና ኬሚካሎች ዝቅ ባሉ ካቢኔቶች/ሼልፎች ውስጥ ማስቀመጥ ወይንም ማስወገድ፤
- በአስቸኳይ ጊዜ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ( መድኃኒት፣ የእጅ ባትሪ ፣ ሬዲዮ፣ አልባሳት) መለየትና ማዘጋጀት፤
- በአደጋው ምክንያት የሚበተነው ቤተሰብ እንዴትና የት ቦታ እንደሚገናኝ አስቀድሞ መወሰን፤ (የስልክ ቁጥሮችን መያዝ)፤
- በቀላሉ ለመፍረስ ተጋላጭ ከሆኑ ህንፃዎችና ቤቶች ራስን ቤተስብ ማራቅና በባለሙያ ምክረ ሀሳብ መሠረት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ መቆየት፤
- በመሬት ንዝረት ክስተት ወቅት
o ባሉበት ተገረጋግቶ መቀመጥና ሊያዙ የሚችሉ ነገሮችን መያዝ እንዲሁም ጭንቅላትን ከጉዳት መከላከል፤
o ከአንዱ ክፍል/ህንፃ ወደ ሌላ ክፍል/ህንፃ መሮጥ/መንቀሳቀስ አለመሞከር፤
o ከሚወድቁ ቁሳቁሶች ራስን ለመከላከል በቀላሉ በማይሰበሩ መከለያዎች (በጠረጴዛ፣ በዴስክና በምሶሶዎቸ፣ በአልጋ) ስር ጎንበስ ብሎ ራስን መከላከል፤
o በመስኮት ወይም በሊፍት ለማምለጥ ወይም ለመውረድ አለመሞከር፤
o ፊትን ወደ በር በማዞር ከመስኮት፣ መስታወቶችና ከከባድ ቁሳቁሶች በመራቅ መቆም፤
o የመሬት መንቀጥቀጡ እስከሚቆም ድረስ ባሉበት ቦታ ተረጋግቶ መቀመጥና አለመንቀሳቀስ፤
o ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሮጥ/መንቀሳቀስ አለመሞከርና የመሬት መንቀጥቀጡ እስከሚቆም ድረስ አለመንቀሳቀስ፤
o ከህንፃዎች፣ ከዛፎች ከግድግዳዎች፣ ከኃይል ማመንጫ መስመሮችና ምሶሶዎች፣ ወዘት በመራቅ ክፍት ቦታ ወይም ሜዳማ በሆኑ ቦታዎች ዝቅ በማለትና ሚዛንን በመጠበቅ መቀመጥ/መቆም፤
- በማሽከርከር ላይ ከሆነ (የንዝረት መጠኑ ከፍተኛ ከሆነ)
o በማሽከርከር ወቅት ክፍት ቦታ መምረጥ፣ በፍጥነት ማቆም፣ ሞተር ማጥፋትና የደህንነት መጠበቂያ ህጎችን ጠብቆ በተሸከርካሪው ውስጥ መቆየት፣
o ተሸከርካሪውን በመተላለፊያ መንገድ ወይም ድልድይ ላይ ወይም በኃይል ማመንጫ መስመር ስር አለማቆም፤
o አስቸጋሪ ሆኖ የግድ ከተሸከርካሪው መውጣት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከተሸከርካሪው በመውጣት ወደ በሜዳማ ቦታ መቆየት፤
- ከመሬት ንዝረት ክስተት በኋላ
- የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ ሊነሱ ከሚችሉ የእሳት አደጋ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የውሃ አደጋዎች እና ሌሎች አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ (የኃይል ማመንጫ ምሶሶዎችና መስመሮች፣ እሳት፣ ኬሚካል፣ መርዛማ ነገሮች፣ ሊወድቁ የሚችሉ ነገሮች) ነገሮች መኖራቸውን ማረጋገጥና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ፤
- የተጎዱ/የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ የመጀመሪያ እርዳታ መስጠት፣ የተጎዱ/የቆሰሉ ሰዎችን በጥንቀቄ እና በፍጥነት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፤
- የህንፃ መሠረቶች፣ ግድግዳዎች፣ ጣራዎች፣ የጭስ መውጫዎች፣ መሰነጣጠቃቸውንና መጎዳታቸውን ማረጋገጥና ሌላ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ፤
- የንዝረቱ ወይም የመሬት መንቀጥቀጡ የሚቀጥል መሆኑ ከታወቀ ወደ ተዘጋጀው ጊዜያዊ መጠለያ መቆየት አካባቢው አደገኛ መሆኑ ከተረጋገጠ ሌላ ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት ከአካባቢው መራቅ፤
- ለአስቸኳይ ጊዜ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፣ ውሃ፣ አልባሳትና መድኃኒት መኖራቸውን ማረጋገጥ፤
- ከዋናው ንዝረት/ መንቀጥቀጥ ተከትሎ ሊከሰት ከሚችል ዳግም የመሬት ንዝረት /መንቀጥቀጥ/ በቂ ዝግጅት ማድረግ፤