የቴሌ ብር መተግበሪያ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 3 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር መፈጸሙን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ ተቋማት በህዝብ ለሚነሱላቸው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ መደረጉ የህዝብ መብት እና ጥቅም እንዲጠበቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በክረምት ወቅት ከወከላቸው ህብረተሰብ የሰበሰቧቸውን ጥያቄዎች ለተቋማት እንዲያቀርቡና ምላሽ እንዲሰጥባቸው እያደረጉ ይገኛል፡፡
በዚህም እስካሁን መብራት ኃይልን ጨምሮ ስድስት ተቋማት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳዳሪነት እንዲሰፍን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ህብረተሰቡ ይህንኑ በማስመልከት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የተመለከቱ ጥያቄዎች ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬይወት ታምሩ በሰጡት ምላሽ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱን በማዘመን የደንበኞቹን ቁጥር እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተለይም አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ ከመደበኛው በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች እያደረሰ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በዚህም እኤአ ከ 2018 ጀምሮ በርካታ ሪፎርሞች ማከናወኑን ጠቁመው የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ የ4ጂ እና 5ጂ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቴሌ ብር አገልግሎት በማስጀመር ለዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት መጣሉን አንስተዋል፡፡
በዚህም ቴሌ ብር መተግበሪያ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 3 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ዝውውር መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂዎቹ የቴሌኮም ተደራሽነትን ከጫፍ ጫፍ ለማዳረስ ከማገዛቸው በላይ የሚሰጠው አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ማስቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም 295 የሚሆኑ አዳዲስ የቴሌኮም ማስፋፊያዎችን በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ አድርገናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ጥራትና ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ቢችልም አሁንም ክፍተት መኖሩን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አንስተዋል፡፡
በልማትና በተለያዩ ምክንያቶች የፋይበር መበላሸት እና የኃይል እጥረት በአንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች ለአገልግሎት ጥራት መጓደል ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም የኔትወርክ ዝርጋታ አለመኖሩን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የፀሃይ ኃይልና ጄኔሬተርን በመጠቀም የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ተደራሽነቱን ለማስፋት ኔትወርክ በሌለባቸው ቦታዎች አዲስ ሳይት በመገንባት አገልግሎቱን ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡