ከሰዓታት በፊት ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥራ የጀመሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ ቀን የአስተዳደር ሥራቸው ቅድሚያ ሰጥተው የሚፈርሙ የአስፈፃሚ ትዕዛዞችን ግልጽ አድርገዋል። እነዚህም በኢሚግሬሽን፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች እና በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡
እነዚህ የአስተዳደር እርምጃዎች በኢሚግሬሽን ቁጥጥር፣ በባሕላዊ እና ማኅበራዊ ፖሊሲዎች እና የሀገር ውስጥ የኃይል ምርት እንዲጠናከር እና የዋጋ ግሽበትን ለማስወገድ በሚያችሉ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።
1 የኢሚግሬሽን እና የድንበር ደህንነት ጉዳዮች
የመጀመሪያው ትዕዛዛቸው የኢሚግሬሽን እና የድንበር ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሀገራቸውን የደህንነት ሁኔታን ለማሻሻል የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ወደ ደቡባዊ የሀገሪቱ ድንበር እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ይህ ድንበር ካሊፎርኒያ፣ አሪዞና፣ ኒው ሜክሲኮ እና ቴክሳስን የሚያዋስነው 3 ሺህ 145 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ድንበር ሲሆን አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር የምትጎራበትበት ነው፡፡
. ዓለም አቀፍ የሽብርተኞች ቡድኖች ላይ የሚካሄደው ዘመቻን ማጠናከር
ትዕዛዙ ትሬን ደ አራጓን የተባሉትን የቬንዙዌላ ወሮበሎችን አሸባሪ ቡድኖች ብሎ የሰየመ ሲሆን ፤ አነዚህን ለመቆጣጠር አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድም ታውቋል።
. የሜክሲኮን የድንበር ቅጥር ግንባታ እንደገና መጀመር
የሀገር ውስጥ ደህንነት እና የመከላከያ መሥሪያ ቤቶች የድንበር ቅጥሩን ግንባታ አጠናቀው ተጨማሪ ሠራተኞችን ለድንበር ቁጥጥር እንዲያሰማሩ ታዝዘዋል።
- ማህበራዊፖሊሲዎች
ሰዎች በተፈጥሮ ባገኙት ባህሪ ላይ ተመሥርው ወንድ ወይም ሴት የሚባሉበትን ህግ የፈረሙ ሲሆን ፤ ከዚህ የሚቃረነው ህግ መሻሩ ተገልጿል፡፡ ይህ እርምጃ ወኅኒ ቤቶችን እና መጠለያዎችን ጨምሮ በፌደራል ተቋማት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን ፤ የሀገሪቱ ዜጎች ከዚህ በኋላ በተፈጥሮ በተሰጣቸው ጾታ ብቻ ይጠራሉ፡፡ በተጨማሪም ጾታን ለመቀየር የሚመደበው የፌደራሉ መንግሥት በጀት አገልግሎት ላይ እንዳይውል ተከልክሏል።
. በብዙዎች ዘንድ እንደ ኮታ በመታየቱ ትችት የገጠውን ብዝሃነት፣ የእኩልነት እና የአካታችነት ፕሮግራምን (DEI) ማስወገድ
ፕሬዚዳንቱ በዘር፣ በጾታ፣ በእምነት፣ በኋላ ታሪክ እና በመሳሰሉት ልዩነቶች ላይ አተኩሮ የሚሠራውን ፕሮግራም ለማስወገድ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የገቡትን ቃል ለመፈጸም ነው ይህን ፕሮግራም የሚሰርዘውን ትዕዛዝ የፈረሙት።
- የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች
. የብሔራዊ ኢነርጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
የሀገር ውስጥ የኃይል ምርት እንዲጨምርና በውጭ የኃይል ምንጮች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የሚያስችል ብሔራዊ የኃይል አዋጅ ፈርመዋል።
. የዋጋ ግሽበትን የተመለከተ የፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለማስወገድ፣ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እና የኢኮኖሚ እድገትን ለመደገፍ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲተገብሩ መመሪያ ለመስጠት የሚያስችል ትዕዛዝም ፈርመዋል።
ለሚ ታደሰ