እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

2 Days Ago 255
እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

ጥምቀት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ኅብረ ብሔራዊ በዓላችን ነው። በሃይማኖታዊነቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማያት ወርዶ፣ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ እናስብበታለን። ይሄም የጠፋውን አዳም ለመፈለግ የተደረገ ጉዞ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም በወደቀበት በእያንዳንዱ ዱካ ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ ተከትሎ ዋጅቶታል። በዚህም አዳምን ወደ ጥንት ክብሩ መመለስ ብቻ ሳይሆን ከጥንቱ የበለጠ ክብር ሰጥቶታል።

ይሄም ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚያስተምረን ብዙ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ የወደቀችበት ብዙ ነው። በእያንዳንዱ በወደቀችበት ውድቀት ተከትለን ማንሣት አለብን። የትርክት፣ የሀገረ መንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የመግባባት ውድቀቶቿን ወደ ትንሣኤዋ መቀየር አለብን።

ክርስቶስ አዳምን ሲያድነው እንዲህ ወይም እንዲያ ማድረግ አለብህ አላለውም። አዳም ዐቅም እንደሌለው ያውቃልና። መዳኑን እርሱ ራሱ ሊያደርገው እንደማይችል ያውቃል። ስለዚህ ክርስቶስ ተገብቶ ፈጸመለት።

ኢትዮጵያችን በዘመናት መከራዎች ደክማለች። በዘመናት ድህነትና ኋላ ቀርነት ተጎድታ ዐቅም አጥታለች። እንዲህ ወይም እንዲያ ማድረግ ነበረባት የሚለው አሁን ለውጥ አያመጣም። መደረግ ያለበትን እኛ ልጆቿ ዛሬ እናድርገው። ስለ ሀገራችን እኛ ቤዛ እንሁን። ቤተልሔም መወለድ ካለብን እንወለድ። በባሕር መካከል መቆም ካለብን እንቁም። መሰደብ ካለብን እንሰደብ፣ መሰቀል ካለብንም እንሰቀል። ነገር ግን ይህ ሁሉ የኢትዮጵያን ትንሣኤ የሚያመጣ ይሁን። ዛሬ እያደረግነው ያለነውም ይሄንኑ ነው።

ጥምቀት ባህላዊ በዓላችንም ነው። የኢትዮጵያ የመስክ ላይ ትዕይንት ማቅረቢያ በዓል ነው። መስኩና ወንዙ ይታይበታል። ልብሳችን እና የወግ ዕቃዎቻችን ለዓለም እናሳያለን። የፀጉር አሠራራችንን እና ዜማዎቻችንን እናቀርባለን። ጥምቀት የኢትዮጵያ ባህል የአደባባይ ሙዝየም ነው።

ብዙ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ይሄንን ወቅት ከሚመርጡበት ምክንያቶች አንዱ ይሄ የአደባባይ ሙዝየም ነው። ከገጠር እስከ ከተማ ፤ ከዳር እስከ መሐል፤ ከውጭ እስከ ሀገር የጥምቀት በዓል የእኛነታችን መገለጫ ነው። 

ጥምቀት ኅብረ ብሔራዊ በዓልም ነው። የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች ለማየት የፈለገ ሰው አንዱ አማራጩ የጥምቀት አደባባይ ነው። በአንድ አደባባይ ሺህ ዓይነቱን ኀብረ ብሔራዊ ማንነታችንን ማየት ይቻላል። የክት የተባለው የባህል ልብሳችን ይወጣል፤ ታይተው የማያውቁ ጌጣጌጦች ብቅ ይላሉ፤ በጥምቀት የኢትዮጵያን መልከ ብዙ ገጽታ ማየት ይቻላል።

እነዚህን የመሰሉ ዕሴቶቻችንን ስላስረከቡን ቀደምቶቻችንን እናመሰግናቸዋለን። ጥምቀት ከተማን ከገጠር ያገናኛል። ብዙዎች ወገኖቻቸውን ለማግኘት ገጠር ይወርዳሉ። የውጭውንም ከሀገር ቤት ያስተሣሥራል። ሚልዮን ወገኖቻችን ጥምቀትን አብረውን ለማክበር ከውጭ ገብተዋል። ይሄም ኅብረ ብሔራዊ ትሥሥራችንን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

የጥምቀትን አስተምህሮ ለሀገር ግንባታ በመጠቀም፤ ባህላዊ እሴቱን በማጎልበት እና ኅብረ ብሔራዊነቱን በማጠናከር በዓሉን እንድናከብር አደራ እላለሁ።

በድጋሚ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥር 10፣ 2017 ዓ.ም


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top