ጥምቀት እና ዝማሬ

2 Days Ago 262
ጥምቀት እና ዝማሬ

የጥምቀትን አከባበር ከሚያደምቁት እና በምዕመኑ ዘንድ ልዩ ክብር ከሚሰጡት ድንቅ ሁነቶች መካከል የጥምቀት ዝማሬ አንዱ ነው።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት የጥምቀት ዝማሬ ጥናትን ከወራት በፊት የሚጀምሩ ሲሆን፣ ከወራት በፊት የጀመሩትን የመዝሙር ጥናት በማጠናቀቅ በከተራ እና በጥምቀት ዕለት በልዩ ኅብር ደምቀው በዝማሬ እና እልልታ እያቀረቡ ታቦታቱን ያጅቡበታል።

የሃይማኖቱ ተከታዮችም በአገልግሎት ልብሶቻቸው ከተዋቡት እና ከየአድባራቱ ተወጣታው በዓሉን በዝማሬ ከሚያደምቁ አገልጋዮች ጋር በመሆን ምስጋናን ያቀርባሉ።

ሁሉም ሰው ጓዳው ሞላ ጎደለ ህይወት ደላም ከፋ በፍፁም ደስታ ምስጋናን ያቀርባል። በዝማሬው ላይ ለመሳተፍ ያመመው ካልጋው ተነስቶ የከፋው ስቆ የደከመ በርትቶ ከያለበት ሁሉ ወደ ዝማሬው ስፍራ ይተማል። ከክፍያ ሁሉ የላቀ ክፍያ በሆነው የዝማሬው በረከት ለመካፈል ፀሐዩ እና ድካሙ ሳይበግረው በአንድነት ፈጣሪውን ያመሰግናል።

ከከተራው ዕለት የሚጀምረው ዝማሬ ታቦታቱን ከጥምቀተ ባሕሩ ወይም ከማደሪያቸው አድርሶ አይቋረጥም እስከ አመሻሽ ይቀጥላል። ደግሞም ነግቶ የጥምቀትን በዓል መታደም የምዕመኑ የነፍስ ጉጉት ነውና ታቦታቱ ከማደሪያቸው ተነስው ቤተ-ክርስቲያን እስኪደርሱ ድረስ በሰዓታት በዝማሬ እና በዕልልታ ያለማቋረጥ ያጅባል። ታቦታቱ ከቤተክርስቲያን ሲደርሱም ዝማሬው ሳይቋረጥ በድምቀት ይቀጥላል።

ገና ወደ ቤተ-ክርስቲያኗ ደጃፍ ሲደርሱ “እልል እልል ደስ ይበለን አጅበን መጣን ታቦተ ህጉን እልል ብላችሁ ተቀበሉን” እያሉ ሲዘምሩ ቀድሞ የደረሱ እና በአካባቢው የሚኖሩ በተለያየ ምክንያት ታቦታቱን ከመነሻው ያላጀቡ ምዕመናን ደግሞ እልል እያሉ ታቦታቱን ይቀበላሉ።

በዚህ መልኩ ነው ታቦታቱ በህብረት ዝማሬ እና እልልታ ታጅበው የሚመለሱት።  ምዕመኑም ለዕለቱ ያደረሰውን ፈጣሪ እያመሰገነ በፍጹም ተመስጦ እና በዝማሬ ያከብራል። የሃይማኖቱ ተከታዮች ያለምንም ድካም ወደ አምላካቸው ምስጋናን እንዲያደርሱ ዝማሬው ኃይል እና ጉልበት የሚሆናቸው ይመስላል፡፡

ዝማሬው ከከተራ እና ጥምቀት ቀጥሎ ባሉት ተከታታይ ቀናትም የሚቀጥል ሲሆን፣ በመላው የሃይማናቱ ተከታዮች የሚናፈቅ ልዩ ሁነት ነው።

በሴራን ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top