የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊየቭ የተመራ ልዑክ ጋር በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ውይይቱ በሀገራቱ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጎልበት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍትና እምቅ ዕድሎችን ለመለየት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ውይይቱ ለወደፊቱ ጠንካራ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት መሰረት የጣለና ሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መንገዶችን የመረመሩበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን የምትልካቸውን ምርቶች ብዝሃነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኗንም ሚኒስትሩ ለልዑካን ቡድኑ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ የከሙን ዘር፣ የተቆላ ቡና፣ ተልባ፣ የፍየል እና የበግ ሥጋ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን በከፊል የተጠናቀቁ የብረትና ቆርቆሮ፣ የሴንትሪፉጅ አካላት እና የኤሌትሪክ ሰርኪዩቶችን የሚከላከሉ መሳሪያዎች እንደምታስገባ ተጠቁሟል።
የአዘርባጃን የገበያ ፍላጎት ከኢትዮጵያ የማምረት አቅም በተለይም ከግብርና እና የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች ጋር የተጣጣመ መሆነም ነው የተገለፀው።
ከውይይቱ በኋላ ሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግና ተጨማሪ እድሎችን መፈተሽ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በቀጣይም ዝርዝር ስምምነቶችን በማድረግ የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ አጋርነትን ለማጎልበት ተስማምተዋል።